መልክዓ - ወንጪ- ደንዲ

መልክዓ - ወንጪ- ደንዲ

ዕውቁ ገጣሚ ነቢይ መኮንን ኢትዮጵያን "ያንቀላፋች ውቢት" ብሎ ተቀኝቶላታል። 

“…ይቺው ናት አለምህ ብቻዋን የተኛች ከዓለም ተደብቃ፣

አኪሯ ቀዝቅዞ፣ "ያንቀላፋች ውቢት" ያንተው የክት ዕቃ…” ይላታል።

ተፈጥሮ ድንቅ ነው። አንዳንድ ገፀ-ተፈጥሮ ግን ይበልጥ ዕፁብ ድንቅ ነው። ተፈጥሮ በራሱ ግራሜ እና ድማሜ፣ ድናቄና ምራኬ፣ ልካፌና ምሳጤ ይፈጥራል። በስነ-አዕምሮ ሊቀ-ማዕምራን ጥናት የውብ ተፈጥሮን ፍቅር ማጣጣም የስነ-ልቦናዊ እና አካላዊ ጤና በረከት ያጎናጽፋል። 

በተፈጥሮ ዓለም መመላለስ መጠነ-ትውስታን ይጨምራል፤ ነገረ-ትኩረትን ያተልቃል፤ ፍርሀት፣ ጭንቀት፣ ብስጭትና ንዴት ይቀንሳል፤ የልብ ምትንና የደም ግፊትን ያመጣጥናል። "ያንቀላፋች ውቢት" ኢትዮጵያ ደግሞ በየፊናው የድንቅ መልክዓ-ምድር ፀጋ ተችሯታል። 

ፀጋዎቿን ወደ ዘላቂ ምንዳ ለመቀየርም ቀዳሚው ነገር ውበቷን በሚገባ ማየትና ማስተዋል ነው። ሁለተኛው ነገር ደግሞ በውበቷ ልክ መሥራት። ቀጣዩ ውበቷን ጠብቆ ማቆየት ይሆናል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እንዳሉትም፤ የማየት፣ የመሥራትና የመጠበቅ ብልጽግና በገበታ ለሸገር፣ በገበታ ለሀገርና በገበታ ለትውልድ ፍንትው ብለው እየታዩ ነው።  

እነዚህ ሦስት የገበታ ፕሮጀክቶች ውበት ብቻ አይደሉም፤ ኃብትም ሕይወትም ጭምር እንጂ። ምክንያቱም የልማት ፕሮጀክቶቹ በትንሽ ጀምሮ ማስፋት፣ ልማትን ማስተሳሰር፣ ዘላቂ የልማት ግቦችን በሚያሳካ አግባብ መሥራት እና ለትውልድ እሴትም አሴትም (ኃብት) ማውረስ የሚሉ መርሆዎችን ያነገቡ ናቸው። 

ለዚህም ነው የገበታ ለሸገር፣ ለሀገርና ለትውልድ ፕሮጀክቶች ውበትም፣ ኃብትም፣ ሕይወትም ናቸው መባሉ። ኢትዮጵያን ካንቀላፋችበት የመቀስቀስ፣ ውበቷንም ለዓለም እንድትገልጥ የማድረግና ለትውልድ የሚተላለፍ ልማት ለማውረስ እየተከናወኑ ካሉ ተግባራት መካከል ወንጪ-ደንዲ አንዱ ማሳያ ነው።  

ወንጪ-ደንዲ ከአዲስ አበባ 135 ኪሎ ሜትር ይርቃል። ሐይቁ ከደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና ከምዕራብ ሸዋ ዞን ርዕሰ ከተሞች ከወሊሶ እና አምቦ አገናኝ ጎዳና ላይ ተኩሎና ተጊጦ ተኝቷል። ወንጪ-ደንዲ የእሳተ ጎመራ አሻራ ነው። በአምቦና ወሊሶ ከተሞች አማካይ ሥፍራ ላይ የከተመው ወንጪ ደንዲ ውብና ማራኪ ገጽታ አለው። መልክዓ - ወንጪ- ደንዲ ዕፁብ ድንቅ የሚያሰኝበት የራሱ መገለጫዎች አሉት። 

ተፈጥሯዊ ብዝኃ-ሕይወቱና ስሪቱ ወንጪ-ደንዲ ሐይቆች ዙሪያ ገባው የውበት ጥግ፣ የተፈጥሮ ቁንጅና ልክ ነው።

የማይጠወልግ ውበት፣ የማይጠገብ ገፀ-ምድር፣ የረቀቀ ማኅበረ-ባህል ባለቤት፣ ምድረ-ገነት የመሰለ የእሳተ ጎመራ ውጤት፣ የገጠሯ ኢትዮጵያ ትዕምርት ነው። ለዚህም ይመስላል የባሕር ማዶ ጎብኝዎቹ "አፍሪካዊ ስዊዘርላንድ" ሲሉ የሚያሞካሹት።

የሐይቁ የከፍታ ቁንጮ ከባሕር ጠለል በላይ 3 ሺህ 386 ሜትር ይደርሳል። ዙሪያው በክብ ተራራ መሀል ክብረ-ሰማይ መስሎ ሲመለከቱት በድስት ውስጥ የረጋ ውሃ ይመስላል።

ዓመቱን ሙሉ ሐመልማላዊ ገጽታ በተላበሱ ከቁጥቋጦ እስከ ግዙፋን ዛፎች ባሸበረቀ የእፅዋት ገመገም ተከቧል። በእንሰትና መሰል ቀልብ ሰራቂ ጎጆዎች ተጊጧል። ደጋማው ወንጪ በጋ ከክረምት አረንጓዴያማነቱ አይከስምም።

የወንጪ - ደንዲ ጎዳና መልክዓ-ምድር እንደ ባቄላ፣ አተር፣ ገብስ፣ ስንዴ እና ጤፍ ላሉ የደጋና ወይና ደጋ ሰብሎች የተመቸ ነው። ተናፋቂ የዱር እንስሳት በወንጪ ሰማይ ሥር ይራኮታሉ፤ ብርቅዬ አዕዋፋት በወንጪ ሰማይ ላይ ይበራሉ። ህልቆ ቢስ የኮሶ ዛፍ፣ ጥድ፣ ወይራ ሌሎችም ሀገር በቀል ዛፎች ይገኛሉ። 

ሥፍራው ለጀብደኛ ጎብኝዎች የተመቸ መዳረሻ ነው። በፈረንጆቹ 2021 (በኅዳር 2014 ዓ.ም) በስፔን ማድሪድ ከተማ በተካሄደው በ24ኛው የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ወንጪ ሐይቅ “ድንቅ የቱሪዝም መንደር” ተሰኝቷል። ይህን ማዕረግ ያገኘው በ70 አገራት ከሚገኙ 174 ኢኮ-ቱሪዝም ሥፍራዎች ተወዳድሮ ነው።

በወንጪ-ደንዲ ዙሪያ ገባ በንቦች የሚወደደው "አንሴ" የሚባል ዛፍ በብዛት በመኖሩ ለንብ ማነብ ሥራ ምቹ ነው። የወንጪ-ደንዲ ማር እጅግ ተፈላጊና ተመራጭ ነው። 

ፍልውኃና ፏፏቴዎች የወንጪ ሐይቅ ጌጦች ናቸው። ሐይቁን ከከበበው ጋራ 44 ያህል ምንጮች ኩልል ብለው ወደ ሐይቁ ይፈሳሉ። ብዝኃ-ሕይወቱ ከባህላዊና ሃይማኖታዊ ፀጋዎቹ ጋር ተሰናስሎ ለዓይንና ለመንፈስ እርካታን ያጎናጽፋል። ለዓይን የሚያጓጓ ማራኪ የሕይወት ቀለብ ነው። 

በነገራችን ላይ ከወንጪ አካባቢ ባህሎች አንዱ ቆጮን ጨምሮ ከእንሰት የሚዘጋጁ ምግቦች ናቸው። ድፎ ዳቦ የሚመስለው "ኦለታ" አንዱ ነው። ብሩንዶ ወይም ክትፎ፣ እንቁላል በአይብ … የማኅበረሰቡ ባህላዊ ምግቦች ናቸው።

የታሪክ እና ቅርስ ሙዳይነቱ

ወንጪ-ደንዲ ሌላው መልኩ በታሪክ እና ቅርስ የበለፀገ ገጽታ መላበሱ ነው። ዝምተኛው ወንጪ ሐይቅ በ14ኛው ክፍለ ዘመን የተተከለውን ታሪካዊና ጥንታዊውን ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም አቅፏል። 

ሐይቁ ሁለት ደሴቶች ያሉት ሲሆን አንዱ  በርካታ ነዋሪዎች ቤታቸውን ቀልሰው የሚኖሩበት ባሕር-ገብ ደሴት ነው። ሁለተኛው ደሴት ደግሞ ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም የሚገኝበት ነው።  

ገዳሙ የታሪካዊ ቅርሶችና የአያሌ ንዋያተ-ቅዱሳት ባለቤት ነው። ከነዚህም መካከል አፄ ዘርዓያዕቆብ ለቤተ ክርስቲያኑ ያበረከቱት ገድለ-ቂርቆስ፣ አፄ ፋሲለደስ ያበረከቱት የብረት መረዋ/ደወል/፣ ዜና ፋሲል የተሰኘ መጽሐፍት ይጠቀሳሉ። 

አፄ ኃይለሥላሴ ደግሞ የሣር ክዳን የነበረውን ቤተክርስቲያን የቆርቆሮ ክዳን አልብሰው አሳንፀዋል።  

በእርግጥ ከደንዲ እና ከወንጪ፣ ከዚያም እስከ ወሊሶ የተዘረጋው ቀጣና ሐመልማላዊ ገፅታ የተጎናጸፈ ብቻ ሳይሆን ሀገር ያፀኑ የጀግኖች አገርም ነው። ለምሳሌ የፊታውራሪ ኃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ (አባ መላ) የትውልድ ቀዬ፣ የአርበኛው ደጃዝማች ከበደ ብዙነሽ የአርበኝነት ሜዳ፣ የደጃዝማች ገረሱ ዱኪ የአርበኝነት ቀዬና የጀግንነት ጎራ፣ የቀድሞው ሠራዊት ዕውቁ የጦር መኮንን ጄኔራል መርዳሳ ሌሊሳ መንደር ነው። የበጋው መብረቅ ጃጋማ ኬሎ እትብት የተቀበረውም ደንዲ አቅራቢያ ነው። የትግል ጫካቸውም ጭልሞ ደን ከአምቦ ቅርብ ርቀት ነው። 

ለኢኮ-ቱሪዝም ቅርበትና መፃዒ ዕድሉ

በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ዞን ዋና ከተማ ወሊሶ በ35 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የወንጪ- ደንዲ ሐይቅ አካባቢው ሰፊ የተፈጥሮ ደን ያለው እንዲሁም ሐይቁ 360 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋትና ከ6 እስከ 78 ሜትር ጥልቀት አለው።

በምርጥ የዓለም የቱሪዝም መንደርነት የተመዘገበው የወንጪ-ደንዲ ኢኮ-ቱሪዝም ለአካባቢው ማኅበረሰብ ኢኮኖሚያዊ አበርክቶ ከፍ ብሏል። 

በወንጪ ኢኮ-ቱሪዝም በጀልባ፣ በፈረስ፣ በማር አምራችነት፣ በቱሪስት ጋይድና በሌሎችም ዘርፎች የተደራጁ በመቶዎች የሚቆጠሩ ማኅበራት ይገኛሉ። 

ኢዜአ ያነጋገራቸው የአካባበው ነዋሪዎችና የቱሪዝም ዘርፍ ተዋናዮች እንደሚሉት ወንጪ ብሩህ ተስፋ ፈንጥቋል። የዛሬ የኑሮ መሠረት፣ ለመጪው ትውልድ ተስፋ ፈንጥቋል። የወንጪ ፕሮጀክት ለእኛም ለልጆቻችንም ትልቅ ተስፋ የሰነቀ ኃብት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ወንጪ የገበታ ለሀገር ሦስት ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ሆኖ ግንባታው ተገባዷል። ድንቅ ተፈጥሮ፣ ታሪክ እና ማራኪ ማኅበረ-ባህል ተዳምረው የወንጪ-ደንዲ ኢኮ-ቱሪዝምን ወደላቀ ደረጃ ያሸጋግሩታል። መፃዒ ተስፋውን ለማየትም መጓጓትን ይፈጥራል።

"ተሼ ሹር" በሚል ስም የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ላይ ያገኘነው ግጥም ወንጪ ደንዲን እንዲህ ይገልፀዋል።

የሰገነት ማዕድ፤ የከፍታ እራት

እንደ ገንፎ ወጪት፤ እንደ ክትፎ ጣባት

ተፈጥሮ እንደ ሳህን፤ ከተራራው አናት

ሐይቅ እንደ ቅቤ፤ የሐኖስ ደም ግባት።

ከወሊሶ ግርጌ፤ ከአምቦ ራስጌ ላይ

የአምላክ እጅ ሥራ፤ የተፈጥሮ ሙዳይ

ምድረ-ፍንትውትዋ፤ የፀጋ እንጉዳይ። 

ጥያቄና መልስ

ኢትዮጵያ ይህን “ድንቅ የቱሪዝም መንደር” ጨምሮ ኃብቶቿን በሚገባ በአስተውሎት ተመልክታዋለች? ከዘላቂ የልማት ግቦች ጋር አስተሳስራ አልምታቸዋለች? ለትውልድ እሴትም አሴትም ለማውረስ በሚሆን መልኩስ አበጃጅታቸዋለች?  "ያንቀላፋች ውቢት" ኢትዮጵያ ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ ሳይኖራት ቆይታለች።

ነገር ግን ባለፉት ጥቂት ዓመታት መንግሥት አዲስ የልማት ዕቅድ ይዞ ብቅ ማለቱ ለጥያቄዎቹ መልስ መስጠት መጀመሩን ያሳያል።

በአሥር ዓመቱ የልማት ዕቅድ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያን ተግባራዊ ለማድረግ አምስት የልማት ምሰሶዎች ተለይተው እየተሰራባቸው ይገኛል። 

እነዚህም ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም፣ ማዕድንና አይ ሲ ቲ ሲሆኑ፤ ደረጃው ይለያይ እንጂ በአምስቱም የኢኮኖሚ አዕማድ(ምሰሶ) ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል።

በውጤታማነታቸው ከሚጠቀሱት መካከልም የቱሪዝም ልማት ተጠቃሽ ነው። በገበታ ለሸገር ተጠንስሶ፣ በገበታ ለሀገር ያደገና በገበታ ለትውልድ እየተንሰራፋ ያለ ሥራ እየተከናወነ ነው። በእርግጥም አንድ ብሎ ጀምሮ ሁለት ማለትን ያሳየ ድንቅ ሥራ ነው። 

በሁሉም ማዕዘናት ልማትን የማዳረስና ፀጋዎችን የማስተሳሰር ተምሳሌትም ነው። በአራቱም አቅጣጫ እንቅልፍ የተጫጫናቸውን ኃብቶች አነቃቅቶ ውበታቸውን የመግለጥ ተሞክሮ የታየበት።   

የልማት ሥራዎችን ከዘላቂ የልማት ግቦች ጋር አስተሳስሮ የመምራት ብቃት የተገለጠበት ሥራ። ለአብነትም ድህነትን ማጥፋትና ጤናማ ሕይወት መፍጠር፣ ምቹ ሥራና የኢኮኖሚ እድገት ማረጋገጥ፣ ፈጠራና መሠረተ-ልማትን ማስተሳሰር፣ ዘለቄታዊነት ያላቸው ከተሞችና መንደሮች መመስረት፣ ዘላቂነት ያለው የኃብት አጠቃቀም ማጎልበት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም እርምጃ መውሰድ፣ የመሬትን ስነ-ምህዳር ለዘላቂ ልማት መጠበቅ የሚሉት ዘላቂ የልማት ግቦች በሚገባ እየተተገበሩ ይገኛሉ።

በአጠቃላይ የቱሪዝም ዘርፉ ላይ እየተካሄደ ያለው ፈጣን የልማት ሥራ ነገን አሻግሮ የተመለከተ ለትውልድ ዕሴትም ኃብትም የማውረስ ድንቅ አካሄድ ነው። 

እናም በየደረጃው ያለ የአስተዳደር መዋቅር፣ የግል ባለሃብቱና ሕብረተሰቡ ይህን ሥራ በማስፋትና የበለጠ ዕሴት በመጨመር የኢትዮጵያን ነገ ዛሬ ላይ መሥራት ይጠበቅበታል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም