ቀጥታ፡

በበልግ ወቅት የአርብቶ አደር አካባቢዎች በቂ ዝናብ ያገኛሉ

አዲስ አበባ፤ ጥር 3/2016 (ኢዜአ)፦በዘንድሮ የበልግ ወቅት የአርብቶ አደር አካባቢዎች ካለፉት አምስት የበልግ ወቅቶች የተሻለ ዝናብ እንደሚያገኙ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅትና የምስራቅ አፍሪካ በየነ መንግስታት (ኢጋድ) ከሰሞኑ የምስራቅ አፍሪካ አገራት በኤልኒኖና ላሊና ተጽዕኖ ስር ይወድቃሉ የሚል መረጃ ማውጣታቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተርና የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ ፕሬዝዳንት ፈጠነ ተሾመ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ኢትዮጵያ የተለያየ የአየር ጠባይ ያላት ሀገር መሆኗን ጠቅሰዋል፡፡ 

ይህን ተከትሎ ኢንስቲትዩቱ የበልግ ወቅት የአየር ሁኔታን ለማወቅ ዓለም አቀፍ ትንበያዎች መሰረት በማድረግ አሁናዊ መረጃዎችን መዳሰሱን ገልጸዋል።  

በዚህም የዓለም አቀፍ የትንበያ ማዕከላት በውቅያኖሶች ላይ የሚኖረው ቅዝቃዜና ሙቀት በኢትዮጵያ አየር ጠባይ ላይ ተጽዕኖ እንዳለው መተንበያቸውን ተናግረዋል።

የሰሜን ምስራቅ፣ የደቡብ አጋማሽ የአገሪቱ አካባቢዎች ሶማሌ ክልልና የደቡብ ኦሮሚያ ዞኖች የባሌ፣ የጉጂ፣ የቦረና ቆላማ ዞኖች እንዲሁም ከፊል የቀድሞ የደቡብ ብሄር ብሄረሰብ ክልሎች ላይ የኢልኒኖ ተጽዕኖ ሊከሰት እንደሚችል መተንበዩን አስታውቀዋል። 

በትንበያው መሰረት በኢትዮጵያ በልግ ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው የሆኑ አካባቢዎች ላይ ኢልኒኖ የሚከሰት ሲሆን የሚያገኙት የዝናብ መጠን ይጨምራል ብለዋል።

ባለፉት አምስት የበልግ ወቅቶች በአርብቶ አደር አካባቢዎች በዝናብ እጥረት ምክንያት ድርቅ ሲከሰት እንደነበር አስታውሰዋል።

ይሁንና በዘንድሮው በልግ እነዚህ አካባቢዎች በቂ ዝናብ የሚያገኙ በመሆኑ ለአርብቶ አደሩ ትልቅ እፎይታ የሚሰጥ ነው ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም