የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ ለመንግስት ብቻ የሚተው አጀንዳ አይደለም - ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ ለመንግስት ብቻ የሚተው አጀንዳ አይደለም - ምሁራን
ጅማ ፤ ጥር 2/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ ለመንግስት ብቻ የሚተው አጀንዳ እንዳልሆነ ምሁራን አመለከቱ።
"የባህር በር ለቀጣናዊ ትስስርና ዘላቂ ሰላም" በሚል ርዕስ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን የተሳተፉበት የፓናል ውይይት ዛሬ ተካሂዷል።
በውይይት መድረኩ የተሳተፋ ምሁራን እንዳሉት፤ የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ ለመንግስት ብቻ የሚተው አጀንዳ አይደለም።
የባህር በር ባለቤትነትና የወደብ ልማት ለቀጣናዊ ትስስርና ለዘላቂ ሰላም ያለውን ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት በጋራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በፓናል ውይይቱ የባህር በርን አስመልክቶ በቀረቡ የመነሻ ጹሑፎች ከወደብ ጋር በተያያዘ ያለውን አገራዊ ጠቀሜታና የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ በንጽጽር ለማሳየት ተሞክሯል።
የባህር በር ለአንድ አገር የኢኮኖሚ እድገትና ብልጽግና ካለው መሰረታዊ ጠቀሜታ አኳያ ተቋማት፣ ተሰሚነቱ ያላቸው ግለሰቦችና ዲፕሎማቶች ሊሳተፉበት ያስፈልጋል ተብሏል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉት በጅማ ዩኒቨርሲቲ የህግና ገቨርናንስ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ራሄል አሰፋ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ህግንና መመሪያን በመከተል በሰጥቶ መቀበልና በዲፕሎማሲ መርህ በሰላማዊ አካሄድ የባህር በር ለማግኘት ጥረት መደረጉ የሚበረታታ ነው።
የባህር በር ለአገር ከሚሰጠው ጠቀሜታ አኳያ ኢትዮጵያ በጋራ ለመልማት ያደረገችው የትብብር ስምምነት የሚደገፍ መሆኑን ተናግረዋል።
"አጀንዳው ትልቅ አገራዊ ጥቅም የሚያመጣልን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይን መንግስት ሲያነሳው ብቻ የምንወያይበት ሳይሆን ተቋማዊና የጋራ መሆን አለበት" ብለዋል።
ኢትዮጵያ ያደረገችውን የባህር በር ስምምነት በተመለከተ ዶክተር ራሔል በሰጡት አስታያየት፤ "የትኛውም አዲስ ነገር ሲወሰንና ሲተገበር ፈተናዎችና ተቃውሞዎች የሚጠበቁ ናቸው"ብለዋል።
"ሆኖም ጉዳዩ ሁላችንንም እንደ አገር ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ በጋራና በአንድነት ለመስራት በቁርጠኝነት መነሳት ይጠበቅብናል" ሲሉ ነው የገለጹት።
ሌላው በጅማ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር ኢድሪስ የባ ለአንድ አገር የባህር በር አስፈላጊነት የተመለከተ ጽሁፍ አቅርበዋል።
በጥናታዊ ጽሑፋቸውም የባህር በር አስፈላጊነትንና ለአንድ አገር የንግድና የኢኮኖሚ ትስስር ያለውን ወሳኝ ድርሻ አመልክተው፤ የባህር በር "ለማግኘት የሚደረግ ጥረት መደገፍ አለበት" ብለዋል።
ኢትዮጵያ ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ አካሄድን ተጠቅማ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት የሚበረታታ ስለመሆኑም ዶ/ር ኢድሪስ ተናግረዋል።