በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚስተዋሉ የአሠራር ክፍተቶች በዘላቂነት መፍትሄ ለመስጠት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚስተዋሉ የአሠራር ክፍተቶች በዘላቂነት መፍትሄ ለመስጠት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 2/2016(ኢዜአ)፦በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚስተዋሉ የአሠራር ክፍተቶች በዘላቂነት መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎች ተዘጋጅተው ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር በተሻሻለው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ረቂቅ ፖሊሲና ባዘጋጀው አዲስ አዋጅ ዙሪያ የባለድርሻ አካላት የግብዓት ማሰባሰቢያ ውይይት ዛሬ አካሂዷል።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ፤ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የጥራት፣ የዘመናዊነትና በወቅቱ ያለመጠናቀቅ ችግሮች ይስተዋላል ብለዋል።
በዚህም ዘርፉ ለአገር እድገት ማበርከት የሚጠበቅበትን አስተዋጽዖ ማበርከት አለመቻሉን ጠቁመው፤ ዜጎች ለሚያነሷቸው የመሠረተ-ልማት ጥያቄ ምላሽ እንዳያገኙ ሆነዋል ነው ያሉት።
ለዚህም የኮንስትራክሽን ዘርፋ የሚመራበት የሕግ ማዕቀፍ ላይ ክፍተት መኖሩን ጠቁመው፤ በተለይም የዘርፉ ተዋንያን መብዛቱን ተከትሎ በዘርፉ ችግሮች እንዲባባሱ ማድረጉን አንስተዋል።
በመሆኑም የኮንስትራክሽን ዘርፉ ያሉበትን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት ዘላቂና አካታች የኢንዱስትሪ ልማትን ማረጋገጥ የሚያስችል ማሻሻያ ማድረግ የግድ አስፈልጓል።
ለዚህም የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ረቂቅ ፖሊሲ መዘጋጀቱን ገልፀዋል።
ፖሊሲው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ባለድርሻ አካላት ከተናጠል ይልቅ ቅንጅታዊ አሠራራቸውን እንዲያጠናክሩ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።
የእውቀት ሽግግር በማከል፤ የመሠረተ-ልማት ፕሮጀክቶችን በጥራትና ባጠረ ጊዜ በማከናወን እንደ አገር ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያግዝ መሆኑንም ተናግረዋል።
የግብዓት አቅርቦትንና የቁጥጥር ሥርዓቱን ማዘመንና መምራት ላይም ጉልህ አስተዋጽዖ እንደሚያበረክት አብራርተዋል።
ፖሊሲው ወደ ሥራ ገብቶ እንዲሁም በአግባቡ ተግባራዊ ተደርጎ የኮንስትራክሽን ዘርፉ በአገሪቱ ምጣኔ ኃብታዊ እድገት የበኩሉን ሚና እንዲጫወት የሁሉም እገዛ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የዘርፉ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው፤ የተዘጋጀው ረቂቅ ፖሊሲና አዋጅ በዘርፉ የነበሩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ያስችላል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።
በተለይም ከግንባታ ጥራት፣ አስተማማኝና ዘመናዊነትን የተላበሰ የመሠረተ-ልማት ግንባታ ባህል እንዲሆን እንዲሁም በዘርፉ ሕገ-ወጥ አሠራርን ለማስቀረትና የሕግ ተጠያቂነትን ለማስፈን እንደሚረዳም ተናግረዋል።
የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ዛሬ በሕግ ማዕቀፎቹ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ግብዓት ሲሰበሰብ የቆየው መድረክ የማጠቃለያ መርሃ-ግብር መሆኑ ተገልጿል።