ቀጥታ፡

የፌዴራል መንግስት ከሶማሌ ላንድ ጋር የጀመራቸውን ሁሉን አቀፍ የትብብር ስምምነቶችን እንደግፋለን - በአማራ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት

ባህር ዳር  ፤ ጥር 2/2016(ኢዜአ):-  የፌዴራል መንግስት ከሶማሌ ላንድ ጋር የጀመራቸውን ሁሉን አቀፍ የትብብር ስምምነቶች ያለ ልዩነት እንደሚደግፉ በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ።

 የጋራ ምክር ቤቱ ዛሬ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ የፌዴራል መንግስት ከሶማሌ ላንድ መንግስት ጋር በመደራደር የደረሰበት ሁሉን አቀፍ የትብብር ስምምነት በአድናቆት ይመለከተዋል።

በየትኛውም ዓለም በመሬት የተከለሉ የባህር በር የሌላቸው አገሮች ከባህር ልማት ብሎም ከመሰረተ ልማት ተደራሽነት ድርብ ፈተና እንደሚገጥማቸው አስታውሶ፤ አገራችን ኢትዮጵያም 120 ሚሊዮን ህዝብ ይዛ ወደብ አልባ ከሆኑ ታዳጊ አገሮች አንዷ መሆኗን ገልጿል።

በአገራችን በባህር በር እጦት በንግድ፣ በትራንዚትና በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ዙሪያ እያመጣ ያለው ሁለንተናዊ ጫና እና ተግዳሮትም የጋራ ምክር ቤቱ በግልፅ የሚገነዘበው ጉዳይ መሆኑን አብራርቷል። 

የባህር በር መዳረሻ ችግር ለከፍተኛ መጓጓዥ ወጪዎች ከመዳረግና ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ አቅምን ከመገዳደር በተጨማሪም በጊዜ ሂደት ከዓለም ገበያዎች የመገለል አደጋም የሚያስከትል እንደሆነ ምክር ቤቱ በፅኑ እንደሚያምን አስታውቋል።

በመሬት የተዘጉ አገሮች መብቶቻቸውን ለማስከበር ከተቀመጡ ህጎች በተጨማሪ በፖለቲካዊ ፍላጎትና ቁርጠኝነት ላይ ተመስርተው በድርድር የሚወስኑ ሁኔታዎች መኖራቸውንም የጋራ ምክር ቤቱ እንደሚረዳ በመግለጫው ገልጿል።

ስለሆነም የፌዴራል መንግስት የአገራችን የባህር በር የማግኘት መብቷን ለማስከበርና ተግባራዊ ለማድረግ ጥረቶች እንደተጠበቁ ሆኖ ከሶማሌ ላንድ ጋር በመደራደር የደረሰበትን ሁሉን አቀፍ የትብብር ስምምነት በአድናቆት እንደሚመለከተው የጋራ ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የጋራ ምክር ቤቱ መንግስት ከሶማሌ ላንድ ጋር የጀመራቸውን ሁሉን አቀፍ የትብብር ስምምነቶች ያለ ልዩነት እንደሚደግፍም አረጋግጧል።

የተጀመረው ድርድርም ፅኑ ውህደት እና ትብብር ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ መላ የኢትዮጵያ ህዝብ የበኩሉን አዎንታዊ ሚና እንዲያበረክት የጋራ ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቧል።

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም