ቀጥታ፡

ዓውደ ርዕዩ ከታሪክ ሂደቶች ተምረን አሁን ያለንበትን ትልም ለማሳካት እና የወደፊቱን የውጭ ግንኙነታችንን በጠንካራ መሰረት ላይ ሆነን እንድናስፈፅም የሚረዳ ነው - አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፤ ጥር 2/2016(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ ርዕይ ከታሪክ ሂደቶች ተምረን አሁን ያለንበትን ትልም ለማሳካት እና የወደፊቱን የውጭ ግንኙነታችንን በጠንካራ መሰረት ላይ ሆነን እንድናስፈፅም የሚረዳ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

"ዲፕሎማሲያችን ለብሔራዊ ጥቅማችን" ከአፍሪካ መዲና እስከ ዓለም መድረክ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ ርዕይ የመክፈቻ መርኃ ግብር ዛሬ ከቀትር በኋላ በሳይንስ ሙዚየም ተካሄዷል።

በዓውደ ርዕዩ መክፈቻ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር እና ሌሎችም ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ዲፕሎማቶች እና ሌሎች ጥሪ የተረደገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።


 

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ ደመቀ መኮንን ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረው እና ብዙ ውጣ ውረድን ያለፈው የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ታሪክ ማስቆጠሩን አስታውሰው ዐውደ ርዕዩ ከዚህ የታሪክ ባህር በጥቂቱ የምናሳይበት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ዝግጅቱ ከታሪክ ሂደቶች ተምረን አሁን ያለንበትን ትልም ለማሳካት እና የወደፊቱን የውጭ ግንኙነታችንን በጠንካራ መሰረት ላይ ሆነን እንድናስፈፅም የሚረዳ ነው ብለዋል።

በየዘመኑ ያጋጠሙንን ፈተናዎች ተቋቁመን ብሔራዊ ጥቅማችንን እያስጠበቅን የመጣነው በህብረታችን እና በጠንካራ አንድነታችን ሲሆን በዚህም የቅርብ ግዜ ፈርጀ ብዙ ጫናዎችን ተቋቁመን የዘለቅነው በህዝባችን ፅናት እና አብሮነት እንደሆነም ገልፀዋል።

አሁን ላይ የሚታዩትን ጫናዎች በመቋቋም ብሔራዊ ጥቅሞችን በዘላቂነት ለማስከበር ውስጣዊ አንድነትን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል።

ካሉብን ተፅዕኖዎች ለመውጣት የድላችን አልፋ እና ኦሜጋ ውስጣዊ ጥንካሬያችን ነው ሲሉ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክትል።

የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ ርዕይ እስከ ጥር 24 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም