ቀጥታ፡

የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ በማጉላት ለቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃት የላቀ አስተዋፅዖ እያበረከቱ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 2/2016(ኢዜአ)፦የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ በማጉላት ለዘርፉ መነቃቃትና የቱሪስት ፍሰት የላቀ አስተዋፅዖ እያበረከቱ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ገለጹ።

የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ፤ የቱሪዝም እንቅስቃሴውን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙኃን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ከቁልፍ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች መካከል አንዱ የሆነው የቱሪዝም ዘርፍ በተለያዩ ምክንያቶች መፈተኑን ገልፀዋል።

በተለይም ኮቪድ-19፣ የሰላምና ፀጥታ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ችግሮች ከዘርፉ ፈተናዎች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በዚህም ምክንያት የቱሪዝም ልማትና እንቅስቃሴው በሚፈለገው ልክ ለሀገር የኢኮኖሚ እድገት ሚና እንዳይኖረው አድርጎታል ብለዋል።

በነዚህ ፈተናዎች ውስጥ ሆኖ በመዳረሻ ልማት ውስንነቶችን ለመቅረፍ በቱሪስት መሠረተ-ልማትና አገልግሎት እምርታን ያመጡ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል።

በተለይም በገበታ ለሸገር፣ በገበታ ለሀገር የተሰሩና በሂደት ላይ ያሉ የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች በዘርፉ ልማት ትልቅ ስኬት የተመዘገበባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ በማጉላት ለዘርፉ መነቃቃት የቱሪስት ፍሰት የላቀ አስተዋፅዖ አበርክተዋል ብለዋል።

የቱሪስት እንቅስቃሴ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች እንዲሰፋ፣ የተረሱና የተደበቁ ፀጋዎችን በማልማት እና ማስተዋወቅ ዓይነተኛ የቱሪስት መዳረሻዎች ማድረግ መቻሉን ነው የገለፁት።

ከመዳረሻ ልማት ባሻገር በዓለም የአየር ጠባይ መቀያየር የተፈጥሮ ኃብት እንዳይጎዳ በማድረግ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማስተዋወቅ እና በገፅታ ግንባታም በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።

የዳያስፖራ የጉዞ ጥሪዎች፣ በዓለም መድረኮች የማስተዋወቅ እንዲሁም ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር በሀገር ገፅታ ግንባታ ዙሪያ የተከናወኑ ተግባራት ውጤት ተገኝቶባቸዋል ብለዋል።

በመሆኑም በገፅታ ግንባታ ረገድ ከዳያስፖራዎች፣ ከዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ እንዲሁም ከግልና የመንግሥት ተቋማት ጋር የተጀመሩ ቅንጅታዊ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉ ተናግረዋል።

እንደ ቪዚት ኢትዮጵያን የመሰሉ መተግበሪያዎችን በመጨመር አገልግሎትን የማዘመን፣ የቱሪዝም ዘርፍ ማበረታቻዎችን ማጠናከርና የዘርፉን ማነቆዎች መፍታት የቀጣይ ትኩረታችን ይሆናል ብለዋል።

የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማሳደግ ባሳለፍነው ዓመት "ልወቅሽ ኢትዮጵያ" ዘመቻ እንዲሁም በትምህርት ቤቶች እና በሌሎች ተቋማት የቱሪዝም ክበባት በመመሥረት ጉብኝትን ባህል የማድረግ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ከባንኮች ጋር በመተባበር ልዩ ማበረታቻ የሚደረግላቸው የጉዞ ቁጠባ የሂሳብ ደብተር እንዲከፈቱ እና ጎብኝዎች በየዓመቱ ሀገራቸውን ተዘዋውረው እንዲመለከቱም ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

በመንግሥት በኩል ለቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ የባለሃብቶችም ትብብርና ተሳትፎ እንዲታከልበት ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም