ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ ታሪኳ ያስመዘገበቻቸውን ስኬቶች አልቆ ለማስቀጠል የጋራ ትብብር ይጠይቃል - ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ ታሪኳ ያስመዘገበቻቸውን ስኬቶች አልቆ ለማስቀጠል የጋራ ትብብር ይጠይቃል - ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ
አዲስ አበባ፤ ጥር 2/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአንጋፋ የዲፕሎማሲ ታሪኳ ያስመዘገበቻቸውን ስኬቶች አልቆ ለማስቀጠል የጋራ ትብብር ያስፈልጋል ሲሉ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።
"ዲፕሎማሲያችን ለብሔራዊ ጥቅማችን" ከአፍሪካ መዲና እስከ ዓለም መድረክ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ ርዕይ የመክፈቻ መርኃ ግብር ዛሬ ከቀትር በኋላ በሳይንስ ሙዚየም ተካሄዷል።
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ብዙ ውጣ ውረድን ያለፈ ነው።
ኢትዮጵያ የረጅም ዓመታት የመንግሥት አስተዳደር ልምድ ያላት፣ ነፃነቷን አስጠብቃ ለዘመናት የኖረች፣ የብዙ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ድርጅቶች መስራች መሆኗን ገልጸዋል።
የአገራት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የውስጥ ማንነትን ማሳያ መሆኑን ገልጸው፣ የዲፕሎማሲ ዐውደ ርዕይው የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚያሳይ መሆኑን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና አገራዊ ክብር ለማስጠበቅ ከመሪዎች እስከ ዲፕሎማቶች ሰፊ ጥረት ማድረጋቸውንም ነው ፕሬዝዳንቷ ያወሱት።
በተለያዩ ዓመታት ኢትዮጵያን በበጎ የሚያስጠሩ የዲፕሎማሲ ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልጸው፣ ነገም ከዚህ የተሻለ ለመስራት በትብብር መስራት ቁልፍ መሆኑን አንስተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው፣ የዲፕሎማሲ አውደ ርዕዩ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ታሪክ ለመዘከር፣ የአሁኑን ለመናገር፣ የመጭውን ዘመን አቅጣጫ ለማመላከት የተዘጋጀ ነው ብለዋል።
በረጅሙ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ታሪክ የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር የባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ትብብሩ ወሳኝ ሚና መጫወቱን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ጫናዎችን ተቋቁሞ ለመውጣት ውስጣዊ አንድነት ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ ርዕይ እስከ ጥር 24 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያል።