ኢትዮጵያ በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ የዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ተቋማት መስራች ናት - ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ የዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ተቋማት መስራች ናት - ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ
አዲስ አበባ፤ ጥር 2/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ የዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ተቋማት መስራች የበርካታ ሰነዶችና ኮንቬንሽኖች ፈራሚ ሀገር መሆኗን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።
"ዲፕሎማሲያችን ለብሔራዊ ጥቅማችን" ከአፍሪካ መዲና እስከ ዓለም መድረክ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት የመክፈቻ መርሀ ግብር እየተከናወነ ነው።
በመክፈቻው ላይ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ብዙ ውጣ ውረድን ያለፈ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የረጅም ስነ-መንግስት አሰራር ልምድ ያላት፣ ነፃነቷን አስጠብቃ ለዘመናት የኖረች፣ የብዙ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ድርጅቶች መስራች መሆኗንም ገልጸዋል።
የሀገራት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የውስጥ ማንነት መገለጫ መሆኑን ጠቁመው ፣ የዲፕሎማሲ ዐውደ ርዕዩ የኢትዮጵያን ታላቅነት ማሳያ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ሀገራዊ ክብር ለማስጠበቅ ከመሪዎች እስከ ዲፕሎማቶች ሰፊ ጥረት አድርገዋልም ብለዋል።
በተለያዩ ዓመታት ኢትዮጵያን በበጎ የሚያስጠሩ የዲፕሎማሲ ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልጸው፣ ነገም ከዚህ የተሻለ ለመፈጸም የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት በትብብር መስራት ይገባል ብለዋል።
ከታሪኩ ጋር ያልታረቀ ህዝብ ብዙ አይሄድም፣ ታሪኩም የተናጋ ይሆናል፣ ለዚህም ተጨማሪ ስራዎች ይጠብቁናል ሲሉም ገልጸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው እንደገለጹት የዲፕሎማሲ አውደ ርዕዩ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ታሪክ ለመዘከር፣ የአሁኑን ለመናገር፣ የመጭውን ዘመን አቅጣጫ ለማመላከት የተዘጋጀ ነው።
በረጅሙ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ታሪክ ብሔራዊ ጥቅማችንን ለማስከበር የተባበረ ዘርፈብዙ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወሳኝ ነበር ብለዋል።
ከታሪክ እንደተማርነው የሀገራችን መጠንከር በበጎ የማይታያቸው አካላት እንዳሉ ገልጸው፣ የኢትዮጵያን አንድነት ለማስቀጠል በጽናት መቆም በአንድነት መዝመት ይገባልም ብለዋል።
ኢትዮጵያ ፅኑ ህዝብ ያላት ብርቱ ሀገር ነች ያሉት አቶ ደመቀ፣ ዓለም አቀፍ ጫናዎችን ተቋቁሞ ለመውጣት ውስጣዊ አንድነታችን ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።