ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ሥምምነት ለማኅበራዊ ኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ ጥቅም አለው- የአሠሪዎች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን 

አዲስ አበባ፤ ጥር 2/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ሥምምነት ለማኅበራዊ ኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ ጥቅም እንደሚኖረው የኢትዮጵያ አሠሪዎች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን አመለከተ።
 
የኢትዮጵያ አሠሪዎች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን በኢትዮጵያና ሶማሌ ላንድ መካከል የተፈረመውን ሁሉን አቀፍ የትብብርና አጋርነት የመግባቢያ ሰነድ አስመልክቶ የድጋፍ መልዕክቱን አስተላልፏል።

በመግለጫውም የኮንፌዴሬሽኑ ዓላማ እንዲሳካ ከሚያስችሉ ጉዳዮች መካከል የቢዝነስ ቱ ቢዝነስ ግንኙነት አንደኛው መሆኑን አመልክቷል።

በመሆኑም በተለይ አሠሪው/ ባለሃብት ከውጭ ሀገር አሠሪዎች ጋር ተገናኝተው የአስመጪና የላኪ ሥራዎች ለመሥራት የወደብ መኖር ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ነው የተመለከተው።

በአሁኑ ጊዜ የሀገራችን የሕዝብ ብዛትና የጠቅላላ የሃገር ውስጥ ምርት በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ለውጭ አገር የሚቀርቡ ምርቶችና /እቃዎች በማኑፋክቸሪንግ፣ በእርሻው ክፍለ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ባለበት አኳኋን ሀገራችን የባህር በር የሌላት መሆኗ በሀገሪቱ ገቢ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ የፈጠረና በገበያ አለመረጋጋት አንዱ መንስኤ ሆኖ ይገኛል ነው ያለው መግለጫው፡፡ 

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የወደብና የባህር በር የምታገኝበትን እድል በመፍጠሩ ከፍተኛ ጥቅም ያለው መሆኑን አውስተዋል።  

ይህ ወደብ የማግኘት ሁኔታ በተለይ በአጠቃላይ ለሀገሪቱ  ማኅባራዊ ኢኮኖሚ  እድገት ከፍተኛ ጥቅም እንደሚኖረው ኮንፌዴሬሽኑ አስገንዝቧል።

አሠሪዎች ነጋዴዎችም ቢሆን የወደብ አገልግሎት ወጪ ከፍተኛ መሆን ሲቸገሩ የነበረበት ሁኔታ ስለሚቀርፍላቸው  ኮንፌዴሬሽናችን ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶታል ነው ያለው መግለጫው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም