ቀጥታ፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም  ጥረት እየተደረገ ነው

ሶዶ ፤ ጥር 2/2016 (ኢዜአ)፡-  በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል  በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ። 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በክልሉ የሚገኙ ተፈናቃዮች የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ እያካሄደ ነው። 

በዚህ ወቅት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እንድሪስ ኤርሚያስ  በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ በተፈጥሮና የሰው ሰራሽ አደጋዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማቋቋም ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦ እየተሰራ ነው። 

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ዘግይቶ የጣለው ዝናብ በሰውና በእንስሳት ላይ የማፈናቀል አደጋ ማድረሱን ጠቅሰው በተለይ በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ ላይ 79 ሺህ 828 አባዎራዎች መፈናቀላቸውን ጠቁመዋል።

በላይኛው የኦሞ ወንዝ ተፋሰስ አካባቢ በጣለው ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ የኦሞ ወንዝ ከመጠን በላይ ሞልቶ በዳሰነች ወረዳ ካሉ 40 ቀበሌዎች ውስጥ በ34ቱ የሚገኙ ነዋሪዎች ማፈናቀሉን አስታውሰዋል። 

ይህንን ተከትሎ ተፈናቃይ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅድ በማውጣት እየተሰራ መሆኑን ምክትል ኮሚሽነሩ ገልፀው እስካሁንም 400 ኩንታል በቆሎን ጨምሮ ከ18 ሺህ ኩንታል በላይ የተለያየ ምግብ ነክ ድጋፍ መቅረቡን አስታውቀዋል።

መንግስታዊ ያልሆኑ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችም ከ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።

ተፈናቃዮቹን በዘላቂነት ለማቋቋም እንዲቻልም ወንዙ የማይደርስበት ደረቃማ ስፍራዎች መረጣ ተደርጎ በ12 መንደሮች ተፈናቃዮችን የማስፈር ተግባር መከናወኑን ገልፀዋል። 

ከክልሉ ጤና፣ ውሃ፣ ትምህርትና መሠል ተቋማት ጋር በመቀናጀት ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ጥረት  እየተደረገ መሆኑንም ምክትል ኮሚሽነሩ አስረድተዋል። 

በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የስደተኞች፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መብቶች የስራ ክፍል ዳይሬክተር እንጉዳይ መስቀሌ በበኩላቸው መድረኩ የተዘጋጀው ከባለድርሻ አካላት ጋር ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ለመምከር መሆኑን አስረድተዋል።


ከሁለት ወራት በፊት ኮሚሽኑ ባከናወነው የመስክ ምልከታ በዳሰነች ወረዳ 11 የተፈናቃይ መጠለያዎችን መመልከቱን ጠቅሰው ችግሩን ለመቅረፍ የተወሰዱ እርምጃዎች በቀጣይ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል። 

በመንግስት አቅም ብቻ ለሁሉም ተፈናቃዮች ተደራሽ መሆን እንደማይቻል አመልክተው መንግስታዊ ያልሆኑ የተራድኦ ድርጅቶች አጋርነታቸውን እንዲያጠናክሩ ማስቻል ይገባል ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም