በሚቀጥሉት አሥር ቀናት የሚኖረው የአየር ሁኔታ የቋሚ ተክሎችን የውኃ ፍላጎት ለማሟላት ይረዳል - ኢዜአ አማርኛ
በሚቀጥሉት አሥር ቀናት የሚኖረው የአየር ሁኔታ የቋሚ ተክሎችን የውኃ ፍላጎት ለማሟላት ይረዳል
አዲስ አበባ ፤ ጥር 2/2016 (ኢዜአ)፡- በሚቀጥሉት አሥር ቀናት የሚኖረው የአየር ሁኔታ ቋሚና እድገታቸውን ያልጨረሱ ተክሎችን የውኃ ፍላጎት ለማሟላት እንደሚረዳ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለፀ።
ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ፤ ዛሬን ጨምሮ ለቀጣይ አሥር ቀናት የሚኖረውን የአየር ሁኔታ ትንበያ ገልጿል።
በዚህም በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው የሆነና ጥምር ግብርና የሚያካሂዱ የደቡብ፣ የደቡብ ምስራቅና የደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው እርጥበት ያገኛሉ።
ይህም ለቋሚና እድገታቸውን ላልጨረሱ ሰብሎች የውኃ ፍላጎት መሟላት፤ በአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ለሚካሄዱ የእንስሳት ልማት ስራዎች እንደሚጠቅም ትንበያው አመላክቷል።
የሚገኘው እርጥበት ለመጠጥ ውኃ አቅርቦት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም እንዲሁ።
በተጨማሪም በመካከለኛው በሰሜንና በሰሜን ምስራቅ አካባቢ የሚኖረው እርጥበት የበልግ እርሻ እንቅስቃሴን ቀድመው ለሚጀምሩ አካባቢዎች ማሳን አስቀድሞ ለማዘጋጀት ጠቀሜታው የጎላ ነው።
ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ፣ አርሲና ምዕራብ አርሲን ጨምሮ በቦረና ዞኖች፤ የሲዳማና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ተገልጿል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አብዛኛው ዞኖች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ተጠቅሷል።
የላይኛውና መካከለኛው ዓባይ ስምጥ ሸለቆ፣ ኦሞ ጊቤ፣ የላይኛው ባሮ አኮቦ፣ ገናሌና ዋቢ ሸበሌ በጥቂት የላይኛው አዋሽና አፋር ደናክል ተፋሰሶች መጠነኛ እርጥበት እንደሚያገኙ ተመላክቷል።
በሌላ በኩል ደግሞ ተከዜ፣ ኦጋዴን፣ አዋሽ፣ ገናሌ ዳዋ ላይ ደረቅና ከፊል ደረቅ እንደሚሆኑ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በመግለጫው ገልጿል።
የቀጣዮቹ አራት ወራት የአየር ፀባይ አዝማሚያ ትንበያ በነገው እለት ይፋ የሚደረግ መሆኑን ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።