የመስኖ ግንባታዎች የምግብ ዋስትናችንን እንድናረጋግጥ እያገዙን ነው- የድሬዳዋ አርሶአደሮች - ኢዜአ አማርኛ
የመስኖ ግንባታዎች የምግብ ዋስትናችንን እንድናረጋግጥ እያገዙን ነው- የድሬዳዋ አርሶአደሮች
ድሬዳዋ ጥር 02/2016 (ኢዜአ)- የመስኖ ግንባታዎች የምግብ ዋስትናችንን እንድናረጋግጥ እያገዙን ነው ሲሉ በድሬዳዋ አስተዳደር የገጠር ነዋሪ አርሶአደሮች አስታወቁ።
በአስተዳደሩ በገጠር የተጀመረው የተቀናጀ የልማት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተመላክቷል ።
ዝናብ አጠር የሆነውን የገጠሩን ህብረተሰብ የምግብ ዋስትና ችግር ለመመለስ የድሬዳዋ አስተዳደር ከፌደራል መንግስት ጋር በመቀናጀት የተለያዩ አነስተኛ የመስኖና የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን በመገንባት የተሻለ ለውጥ እንዲመጣ እየሰራ ይገኛል።
ሰሞኑን በ300 ሚሊየን ብር የሚጠጋ በጀት ተገንብተው ወደ ስራ የገቡት ስድስት የአነስተኛ መስኖና ሶስት የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች የዚህ ማሳያ መሆናቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የገለፁ አርሶአደሮች ተናግረዋል።
የቢሻን በሄ ገጠር ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ዲኔ ጀማል እንደገለጹት፤ መንግስት በአመት አነስተኛ ዝናብ የሚያገኘውን የገጠሩ ህብረተሰብ ከድህነት ለማውጣት እያስፋፋ የሚገኘው የመስኖ ፕሮጀክት የገጠሩን ህብረተሰብ ተስፋ አለምልሟል።
በቀበሌው ከሶስት አመት በፊት በተገነባ የመስኖ ፕሮጀክት በመጠቀም ቡና፣ ፖፖያ፣ አፕል፣ ማንጎ፣ ሙዝ፣ ቲማቲምና ሽንኩርት በአመት ሁለት ጊዜ በማምረትና ለገበያ በማቅረብ የተሻለ ገቢ እያገኘሁና የምግብ ዋስትናዬን በማረጋገጥ ላይ ነኝ ብለዋል።
አርሶአደር መሐመድ አልይ በበኩላቸው አስተዳደሩ የሚሰራቸው የልማት ፕሮጀክቶች የገጠሩን ህብረተሰብ ሰርቶ የመለወጥ መንፈስ አነቃቅቷል ብለዋል።
ከመስኖ ፕሮጀክት በተጨማሪ የውሃ መሳብያ ፖንፕና በሶላር የሚሰራ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ መሆናችን የምግብ ዋስትናችንን ለማረጋገጥ እንድንተጋና ውጤት እንድናስመዘገብ አስችሏል ሲሉ ገልፀዋል ።
አሁን በገጠር እየተሠሩ በሚገኙ ለልማት አውታሮችን በመጠቀም በሁለት አመታት ውስጥ ከተረጂነት በመውጣት ለሌሎች አርአያ እንደሚሆኑ የገለጹት ደግሞ አርሶአደር ሙክታር አደም ናቸው።
ከመስከረም ወር ጀምሮ በማህበር ተደራጅተን ያመረትነው ቲማቲም ብቻ ጥሩ በገበያ ዋጋ ካወጣልን በኑሯችን ላይ ጅምር ለውጥ ያመጣል ብለዋል።
አስተዳደሩ በተጎራባች ቀበሌዎች በገነባቸው የመስኖ ፕሮጀክቶች በመጠቀም ኑሯቸውን የለወጡ አርሶአደሮችን ተመልክተን እኛም በቡድን ተደራጅተን ከቆፈርነው የውሃ ጉድጓድ አትክልትና ፍራፍሬ እያመረትን እንገኛለን የሚሉት አርሶአደር አብዲ አደም በበኩላቸው ቢሆንም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የመስኖ ተጠቃሚ መሆን አለብን ብለዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር የመጠጥ ውሃ ጥያቄያችን ምላሽ በመስጠቱ ተደስተናል፤ ሴቶች ልክ እንደ ወንዶቻችን በልማት ስራ በመሳተፍ የተሻለ ለውጥ የምናመጣበት ጊዜ ላይ ደርሰናል" ያሉት ደግሞ የጅጋ ቀበሌ አርሶአደር ወይዘሮ ኑሪያ አህመድ ናቸው።
የድሬዳዋ አስተዳደር የግብርና ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኑረዲን አብደላ እንዳሉት የገጠሩን ህብረተሰብ መሠረታዊ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለማቃለል እየተሰራ ነው።
አነስተኛ መስኖ ፕሮጀክቶችን በማስፋት በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመረውን አበረታች ለውጥ ዳር ለማድረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።