ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን የአገራቸውን ባህልና እሴት የሚያውቁበት ሁነቶች ተዘጋጅተዋል - ኢዜአ አማርኛ
ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን የአገራቸውን ባህልና እሴት የሚያውቁበት ሁነቶች ተዘጋጅተዋል
አዲስ አበባ፤ ጥር 2/2016(ኢዜአ)፦ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን የአገራቸውን ባህል፣ እሴትና ጣዕም በአግባቡ የሚያውቁበት የተለያዩ ሁነቶች መዘጋጀታቸው ተገለጸ።
ሁለተኛው ትውልድ- ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲመጡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የተደረገውን ጥሪ ተከትሎ በመጀመሪያው ዙር በርካቶች እየገቡ መሆኑን የዓብይ ኮሚቴው አስተባባሪዎች አስታውቀዋል።
መንግሥት አገራቸውን እንዲጎበኙ ጥሪ ያደረገላቸው በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን በቆይታቸው የሚሳተፋበትና ከአገራቸው ጋር ያላቸውን ትስስር የሚያጎለብቱበት ልዩ ልዩ ዝግጅቶች መሰናዳታቸው ታውቋል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ፤ የሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲመጡ በተቋቋመው ዓብይ ኮሚቴ በኩል የተለያዩ ሥራዎች እየተሰራ ነው ብለዋል።
አገሩን ያወቀ አገሩን የወደደ ትውልድ መፍጠር የሚያስችል፣ የትውልዱን ልዩ ባህሪ ታሳቢ ያደረጉ ዝግጅቶች እንዲሁም ለአገራቸው ማበርከት የሚፈልጉትን ራዕይ እውን ማድረግ የሚያስችሉ መርሃ-ግብሮች መዘጋጀታቸውንም ነው ያብራሩት።
በመጀመሪያው ዙር ወደ አገራቸው እየገቡ ላሉ ኢትዮጵያውያን "በኢትዮጵያ ሳምንት" ከጉብኝት ፓኬጅ ጀምሮ የኢትዮጵያን ባህል ጣዕምና እሴት በአግባቡ የሚያውቁበት የተለያዩ ሁነቶች ተዘጋጅተውላቸዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያን የዕደ-ጥበብ ውጤቶች እንዲያውቁ የሚደረግበትና የኢትዮጵያን ድምፆች በተለያየ የሙዚቃ መሳሪያዎች የሚተዋወቁበት ሁነት እንዳለ አመልክተዋል።
ትውልዱ በራሱ ኃብት እንዲኮራና እንዲጠቀም የተለያዩ ባህላዊ አልባሳትና የዕድ- ጥበብ ውጤቶች አውደ- ርዕይ የተዘጋጀ ሲሆን፤ ኢትዮጵያን ለዓለም ገበያ የማስተዋወቅ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።
ከዚህ ባለፈ የኢትዮጵያን ምድረ-ቀደምትነት የሚያረጋግጡ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች መዘጋጀታቸውንም እንዲሁ።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሃመድ እድሪስ በበኩላቸው፤ ለሁለተኛው ትውልድ አባላት የተደረገው ጥሪ ከአገራቸው ጋር ያላቸውን ቁርኝት ለማሳደግና ለአገራቸው ያላቸውን አመለካከት ለመቀየር ያስችላል ብለዋል።
ጥሪውን ተከትሎ በርካታ የሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እየገቡ መሆኑንም ገልፀዋል።
በማደጎ ወደ ተለያዩ አገራት የሄዱትን ጨምሮ እዚያው ተወልደው ያደጉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ- ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ለመምጣት ያሳዩትን ተነሳሽነት አድንቀዋል።
በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአገራዊ ጉዳዮች ላይ እንዲሳተፉ ተደራሽ ከማድረግ አኳያ ለሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን የቀረበው ጥሪ ከፍተኛ ሚና አለው ነው ያሉት።
በተለያዩ አገራት ከ20 በመቶ በላይ የሚሆኑ የሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ ትውልዱ የማንነት ቀውስ ውስጥ እንዳይገባ እንዲህ ዓይነት ጥሪዎች ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ፤ የተለያዩ አካላት ከቦሌ ዓለምአቀፍ አየር ማረፊያ ጀምሮ ለሚመጡ እንግዶች አስፈላጊውን ትብብርና እገዛ እያደረጉ መሆኑን አመልክተዋል።
ቆይታቸውም የተሳካ እንዲሆን ሰላምና ፀጥታን ጨምሮ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።