ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት የመክፈቻ መርሀ ግብር እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 2/2016 (ኢዜአ)፦ "ዲፕሎማሲያችን ለብሔራዊ ጥቅማችን" ከአፍሪካ መዲና እስከ ዓለም መድረክ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት የመክፈቻ መርሀ ግብር እየተከናወነ ነው።

በመርሀ ግብሩ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ አንጋፋ ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል።

ተቋማዊ አደረጃጀት ከያዘ ወዲህ 116 ዓመታትን የተሻገረው የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ በበርካታ ውጣ ውረዶች አልፎ ውጤት እያስመዘገበ እዚህ ደርሷል።

ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ ተቋማት እስከ ቀጣናዊ ትስስር ተቋማት ምስረታ ከመስራችነት እስከ ንቁ ተሳታፊነት የጎላ አበርክቶ አድርጋለች።


 

ተለዋዋጭ የሀይል አሰላለፍ፣ ፈርጀ ብዙ ዲፕሎማሲ፣ አዳዲስ ዓለም አቀፍ አጀንዳዎች በተበራከቱበት የዘመኑ ዲፕሎማሲ ኢትዮጵያ አካታችነትን፣ ወዳጅ በማብዛት፣ ተደማጭነትን በመጨመር እና ተደራሽነትን በማስፋፋት ብሔራዊ ጥቅሟን ማዕከል አድርጋ እየሰራች ነው።

ከሊግ ኦፎ ኔሽን አባልነት እስከ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መስራችነትና መሪ ተዋናይነት ተሳትፋለች።

ኢትዮጵያ በቀጣቀናው ሰላምና መረጋጋት ተፈጥሮ በጋራ መልማትን ግብ በማድረግ ለምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ምስረታ የበኩሏን ተወጥታለች።

በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ከጎረቤት ሀገራት እስከ ኮሪያ፣ ከአፍሪካ እስከ ዓለም መድረክ ሰንደቋን አላማዋን  ከፍ አድርጋ አውለብልባለች።

ክፍለ ዘመን በተሻገረው ረጅሙ የዲፕሎማሲ ታሪክ ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ተደማጭ፣ በቀጣናው ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆና ቀጥላለች።

በአረንጓዴ ዲፕሎማሲ፣ በኢኮኖሚ፣ በህዝብ ለህዝብ፣ በጤናና በጠፈር እንዲሁም ዘመኑ በሚጠይቀው ዲፕሎማሲያዊ ሁነት ሁሉ ውጤታማ ስራ አከናውናለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰላም ዲፕሎማሲ የሰላም ኖቬል ተሸላሚ የሆኑበትና በአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ተቀባይነት ያገኙበት ለዚህ ተጠቃሽ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም