ያለንበትን ጂኦ ፖለቲካዊ ቀጣናን የሚመጥንና የወደፊት የፀጥታ ደህንነት ሁኔታን አሻግሮ የሚያይ የወታደራዊ መረጃ ተቋም እየተገነባ ነው - ጀኔራል ጌታቸው ጉዲና - ኢዜአ አማርኛ
ያለንበትን ጂኦ ፖለቲካዊ ቀጣናን የሚመጥንና የወደፊት የፀጥታ ደህንነት ሁኔታን አሻግሮ የሚያይ የወታደራዊ መረጃ ተቋም እየተገነባ ነው - ጀኔራል ጌታቸው ጉዲና
አዲስ አበባ፤ ጥር 02/2016(ኢዜአ)፦ ያለንበትን ጂኦ ፖለቲካዊ ቀጣና የሚመጥንና የወደፊት የፀጥታና ደህንነት ሁኔታን አሻግሮ የሚያይ የወታደራዊ መረጃ ተቋም እየተገነባ ነው ሲሉ ጀኔራል ጌታቸው ጉዲና ገለጹ።
የመከላከያ መረጃ ዋና መምሪያ እና በመከላከያ ትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ የመረጃ ኮሌጅ ያሠለጠኗቸውን የመረጃ ሙያተኞች እና አመራሮች አስመርቀዋል።
በምርቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ጀኔራል ጌታቸው ጉዲና ያለንበትን ጂኦ ፖለቲካዊ ቀጠና የሚመጥን ብቃት ያለው የመረጃ ተቋም ለመገንባት እየሠራን ነው ብለዋል።
ዘመኑ የደረሠበትን የመረጃ ቴክኖሎጂ መጠቀም የሚችል የሰው ኃይል ማፍራት ቀዳሚ ተግባራችን ነው ያሉት ጀኔራል መኮንኑ የመረጃ አሰራር አደረጃጀቶችን በማዘመን አቅም ያለው የመረጃ ተቋም እየገነባን እንገኛለን ሲሉም ተናግረዋል።
ሁለንተናዊ ወታደራዊ ዝግጁነታችንን በማጠናከር የሚገጥመንን ጦርነት የሚቀለብስ ኃይል ከማብቃት በተጨማሪም ወደፊት ሊያጋጥሙ የሚችሉ የደህንነት ስጋቶች ተለይተው እየተሠሩ ስለመሆኑም ጀኔራል ጌታቸው ጉዲና ገልፀዋል።
ጀኔራል መኮንኑ የሀገራችንን ክብር ሊያስጠብቅ የሚችል የመረጃ ሙያተኛ የማብቃት ሒደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀው ዛሬ የተመረቁ የመረጃ ሙያተኛ እና አመራሮች ያላቸውን ልምድና ክህሎት ካገኙት እውቀት ጋር ቀምረው ግዳጃቸውን በቁርጠኝነት ሊፈፅሙ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በመርሐግበሩ ላይ የፌዴራል የፀጥታና የደህንነት ተቋማት አመራሮች፣ ጀኔራል መኮንኖች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መገኘታቸውን ከመከላከያ ሠራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።