ቀጥታ፡

የባህር በርን የማግኘት ጥያቄ ህጋዊ መሰረት ያለው በመሆኑ ተግባራዊ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ሊጠናከር ይገባል-ምሁራን 

ሚዛን አማን ፤ ጥር 02/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጥያቄ የሕግ መሠረቶች ያሉት በመሆኑ ተግባራዊ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ምሁራን ገለጹ።

ከሶማሌላንድ ጋር የተደረሰው የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ በጋራ የመልማት መርህን ተግባራዊ ያደረገ መሆኑን የገለፁት ምሁራኑ ውጤታማ እንዲሆንም አለም አቀፍ ህጎችን ባማከለና በሰጥቶ መቀበል አካሄድ ሊከናወን እንደሚገባም አመላክተዋል።

በዩኒቨርሲቲው የሕግ ትምህርት ክፍል መምህር አዳነ ኮርቦ እንዳሉት፤ ለኢትዮጵያ የባህር በር አግኝቶ ወደብ የመጠቀም ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም።

"የትኛውንም አዋጭና ሰላማዊ የሆነ መንገድ ተከትሎ ሀገራዊ የማደግ ፍላጎትን ሊያግዝ የሚችል ውሳኔ ላይ መድረስ ተገቢ እና ለትውልድ የተሻለ ነገርን የሚያመጣ ጉዳይ ነው" ብለዋል።

የባህር በሩ ከሀገራችን ግዛት ውጭ ያለ ቢሆንም ጥያቄው ህጋዊ መሰረት ያለው ነው ያሉት መምህር አዳነ በመሆኑም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሕጎችን መሠረት አድርጎ መሥራትና ጥረቶቹ ሊጠናከሩ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ለዚህም ድንበር ተሻግሮ የተፈጥሮ ሀብትን የመጠቀም መብት በሌሎች ሀገራትም የተለመደና እየተተገበረ ያለ በመሆኑ ኢትዮጵያም ይህንን ሥርዓት ተከትላ የመጠቀም መብቷ ሊረጋገጥ ይገባል ነው ያሉት።

ሌሎች ሀገራትን በማይጎዳ መልኩ በሰጥቶ መቀበል መርህ ስምምነት ፈጽሞ መልማትን የሚከለክል ሕግ አለመኖሩን አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት እያደረገች ያለው እንቅስቃሴ በሰላማዊ መንገድ ወይም በስምምነት ማዕቀፍ የሚከወን በመሆኑ የባህር በር ያላቸው አገራት ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ የባህር በር እንዲሰጡ የሚያስችል ጤነኛ አካሄድ ነው ብለዋል።

ሰጥቶ መቀበል በቢዝነስ ሕግ በሁለቱ ተግባቢዎች መልካም ፈቃድና አዋጭነት ላይ ብቻ ተመርኩዞ የሚፈጸም መሆኑን የገለጹት ደግሞ በዩኒቨርስቲው የምጣኔ ሀብት መምህር ይስሐቅ ንጉሴ ናቸው።

ይህን ስምምነት ኢትዮጵያ ከሶማሌ ላንድ ጋር በግልጽ አሠራርና ሕግን በተከተለ መልኩ ፈጽማለች ነው ያሉት።

እየተገኘ ያለውን መልካም ነገር ሥርዓትና ሕጋዊ መሠረት ያለው መሆኑን ተገንዝቦ መሥራት እንጂ ለሌላ አጀንዳ አሳልፎ መስጠት አይገባም ብለዋል።

የሀገራት ጠንካራ የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንኳ ሰጥቶ መቀበል ላይ የተመረኮዘ ሲሆን ይህ የቀይ ባህር በር የማግኘት ጉዳይም ከዚህ ያፈነገጠ አለመሆኑን ተናግረዋል።

የጉዳዩ ባለቤቶች ኢኮኖሚያዊ ሚዛናቸውን ጠብቀው በሚያደርጉት ስምምነት እንጂ የሌላ አካል ጫናና ግፊት እንዲታከል የቢዝነስ ሕግ እንደማይፈቀድ አመላክተዋል።

ሶማሌላንድ የባህር በርን ሰጥታ ከኢትዮጵያ የምትወስደው ኢኮኖሚያዊ ድርሻ እንደሚኖር የገለፁት ምሁሩ ኢትዮጵያ ወደብ ገንብታ ስትጠቀም የምጣኔ ሀብት ዕድገት እንደሚኖራት ታሳቢ ያደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ያላትን ሀብት ለዓለም ገበያ በማቅረብና የውጭ ምርቶችን ያለ ብዙ ወጪ በማስገባት መጠቀም እንድትችል ለስምምነቱ ስኬት ሁሉም ኢትዮጵያውያን ባሉበት የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ቀጠናዊ የጋራ ተጠቃሚነትን መርህ አድርጋ እየሰራች በመሆኑ ስምምነቱን የቀጠናው ሀገራት መደገፍ እንዳለባቸውም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም