በትግራይ ክልል በሁለት ቢሊዮን ብር ወጪ የኤሌክትሪክ ኃይል ማሻሻያ ፕሮጀክት እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል በሁለት ቢሊዮን ብር ወጪ የኤሌክትሪክ ኃይል ማሻሻያ ፕሮጀክት እየተካሄደ ነው
መቀሌ ፤ጥር 2/2016 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በትግራይ ክልል በሁለት ቢሊዮን ብር ወጪ የኤሌክትሪክ ኃይል ማሻሻያ ፕሮጀክት እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ።
በክልሉ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ግርማይ ግደይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በፕሮጀክቱ የጊዜያዊ አስተዳደሩን የኤሌክትሪክ አቅርቦት የሚያሻሽሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።
ፕሮጀክቱ በተለያዩ ችግሮች የሚከሰተውን የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ለማስቀረት እንደሚያስችል አስታውቀዋል።
በዚህም በጊዜያዊ አስተዳደሩ በእንጨት ምሰሶዎች መውደቅና በትራንስፎርመሮች መቃጠል ሳቢያ የሚያጋጥመውን የኃይል መቆራረጥ ችግር ለመከላከል ይረዳል ብለዋል።
በዚህም በጊዜያዊ አስተዳደሩ በኃይል ማስተላለፊያነት ያገለግሉ የነበሩ የእንጨት ምሰሶዎች በኮንክሪት እየተቀየሩ መሆኑን አስረድተዋል።
ፕሮጀክቱ ትራንስፎርመሮችን መጠገንና መቀየርን እንደሚያካትትም አቶ ግርማይ አብራርተዋል።
በፕሮጀክቱ በ14 ማህበራት የተደራጁ 1ሺህ 500 ወጣቶች ሥራ እንደተፈጠረላቸውም ገልጸዋል።
የዲስትሪክቱ ከፍተኛ መሐንዲስ ኢንጂነር አብርሃም ከበደ በ950 ኪሎ ሜትር ላይ የሚገኙ የእንጨት ምሰሶዎችን በኮንክሪት እየተቀየሩ መሆኑን ገልጸው፤ እስካሁንም ሥራው 90 በመቶ መከናወኑን ተናግረዋል።
እየተቀየሩ ያሉት ምሰሶዎች ከ30-40 ዓመታት አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችሉም አብራርተዋል።
የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት እንዲሰጡም ኅብረተሰቡ ሊጠብቃቸውና ሊንከባከባቸው እንደሚገባም ኢንጂነር አብርሃም ጠይቀዋል።
በእንደርታ ወረዳ የጨለቆት ቀበሌ ነዋሪዎች አቶ ረዳኢ በርሄና አቶ ንጉሥ ገብረ ሥላሴ በሰጡት አስተያየት፤ በአካባቢያቸው የነበረው የእንጨት ምሰሶዎች በመውደቃቸው በኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት መቆራረጥ ይቸገሩ እንደነበር ገልጸው፣ አሁን ግን ምሰሶው በኮንክሪት በመቀየሩ የሃይል አቅርቦቱ መሻሻሉን ተናግረዋል።