ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ዕድገት ቀጣይነት ይኖረዋል- አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ 

አዲስ አበባ፤ ጥር 02/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ዕድገት በአውሮፓውያኑ አዲስ አመትም 6 ነጥብ 2 በመቶ ሆኖ እንደሚቀጥል የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ አመለከቱ።

አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ከደቡብ አፍሪካው ሲ ኤን ቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት በበርካታ ጫናዎች ውስጥም ሆኖ ላለፉት ሶስት አመታት በዕድገት መዝለቁን ገልጸዋል።

የአለምአቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) በዓለም ካሉ ምርጥ አስር የምጣኔ ሀብት እድገቶች ስድስቱ በአፍሪካ አህጉር ይሆናሉ ሲል ያስቀመጠውን ትንበያ በመጥቀስ  ኢትዮጵያ ከአይቮሪኮስት በመቀጠል ሁለተኛውን እድገት እንደምታስመዘግብ አስረድተዋል። 

አለምአቀፍ ስጋት የነበረውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ በሰሜናዊ ኢትዮጵያ የነበረው ግጭት ብሎም የሩሲያና የዩክሬን ጦርነትን ጨምሮ በሌሎች ውጫዊ ዘርፈ ብዙ እንቅፋቶች የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብት በእጅጉ ሲፈታተኑት መቆየታቸውን አብራርተዋል።

በተጠናቀቀው የአውሮፓውያኑ 2023 የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት በ6 ነጥብ 2 በመቶ ማደጉን እና በተያዘው ዓመትም በተመሳሳይ ዕድገቱ እንደሚቀጥል የዓለም የገንዘብ ድርጅት መረጃን ዋቢ አድርገው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት አሁንም በግብርና ላይ በመመስረቱ መንግስት ዕድገቱን በማምረቻ በአገልግሎት ብሎም በመሰረተ ልማት ዘርፎች ላይ ለማድረግ አስቻይ ሁኔታዎችን እየፈጠረ መሆኑን ያብራሩት አቶ ዘመዴነህ ላለፉት 16 ዓመታት የተከማቸውን የዋጋ ግሽበት ለማስተካከል የሚረዱ ተከታታይ የፖሊሲ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው ብለዋል።

አቶ ዘመዴነህ ኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብታዊ የመዋቅር ለውጥ በማድረግ ገቢ ምርቶችን በመቀነስና ወጪ ምርቶችን በማሳደግ በኢንዲስትሪና በአገልግሎት ዘርፎች ላይ እየሰራች ያለችው ምጣኔ ሀብታዊ አቅሟን አስተማማኝ ቁመና ላይ ለማድረስ መሆኑን አብራርተዋል።  
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም