ከጉጂ ዞን ባለፉት ሁለት ወራት ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ19 ሚሊዬን ብር በላይ ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
ከጉጂ ዞን ባለፉት ሁለት ወራት ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ19 ሚሊዬን ብር በላይ ተሰበሰበ
ጉጂ ፤ጥር 2/2016 (ኢዜአ) :- ከጉጂ ዞን ባለፉት ሁለት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ19 ሚሊዬን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የዞኑ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡
ከዞኑ ህዝብ ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ለግድቡ ግንባታ በአይነት፣ በስጦታና በቦንድ ከ19 ነጥብ 9 ሚሊዬን ብር በላይ መሰብሰቡ ተመልክቷል፡፡
ከጉጂ ዞን ህዝብ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚደረገው ድጋፍና ትብብር ተጠናክሮ መቀጠሉንም ጽህፈት ቤቱ ገልጿል፡፡
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ዴንቆ በተያዘው ዓመት ለግድቡ ግንባታ ከዞኑ 17 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማሰባሰብ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡
ሆኖም በዞኑ ከህዳር 1 እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2016 ዓ.ም ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማስፈጸሚያ የሚውል የሀብት ማሰባሰብ ስራ ሲከናወን መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
እስካሁን ከዞኑ ሁሉም ከተሞችና ወረዳዎች 19 ነጥብ 9 ሚሊዬን ብር በላይ አጠቃላይ ድጋፍ መሰብሰቡን ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ ውስጥ 19 ሚሊዬን 191 ሺህ ብር ከቦንድ ሽያጭ የተሰበሰበ ሲሆን ቀሪው 758 ሺህ ብር ከባለሀብቶችና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በአይነትና በስጦታ መልክ የተበረከተ ነው ብለዋል፡፡
ከዞኑ ህዝብ እስካሁን የተሰበሰበው አጠቃላይ ገቢ ከዓመታዊ እቅዱ በ2 ሚሊዬን 950 ሺህ ብር የሚጠጋ ብልጫ ያለው እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
በቦንድ ግዥው አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮች፣ የመንግስት ሰራተኞችና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በመሳተፍ ላይ ናቸው ብለዋል፡፡
የዞኑ የአዶላ ከተማ ነዋሪ አቶ ቦኮ በለኮ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ቦንድ ከገዙ ከአዶላ ወረዳ መንግስት ሰራተኞች መካከል አንዱ ናቸው፡፡
ባለፉት ዓመታት የ6 ሺህ ብር በላይ ቦንድ መግዛታቸውን ገልጸው ዘንድሮም በተመሳሳይ ለግድቡ ግንባታ ማስፈጸሚያ የ1 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን አስታውቀዋል፡፡
የዚሁ ከተማ ነዋሪና የመንግስት ሰራተኛው አቶ ሙላት ከበደ፣ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ አምስት ጊዜ ቦንድ መግዛታቸውን ገልጸዋል።
በዚህኛው ዙርም የ1 ሺህ ብር ቦንድ የገዙት አቶ ሙላት የግድቡ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል፡፡
የዘንድሮን ጨምሮ ለግድቡ ግንባታ እስካሁን ድረስ የ13 ሺህ 473 ብር ቦንድ መግዛታቸውን አስታውሰዋል፡፡