ስምምነቱ ለቀጣናዊ ትስስርና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ አዎንታዊ ሚና የሚጫወት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ስምምነቱ ለቀጣናዊ ትስስርና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ አዎንታዊ ሚና የሚጫወት ነው
ጅማ፤ ጥር 2/2016(ኢዜአ):- ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የፈጸመችው ስምምነት ለቀጣናዊ ትስስርና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ አዎንታዊ ሚና የሚጫወት መሆኑ ተገለጸ።
ዛሬ በጅማ ዩኒቨርሲቲ 'የኢትዮጵያ የባህር በር ለቀጣናዊ ትስስርና ዘላቂ ሰላም' በሚል ምሁራን ባቀረቡት የመነሻ ጽሑፍ የፓናል ውይይት ተደርጓል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የጅማ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀማል አባፊጣ፣ ኢትዮጵያ በገጠማት የታሪክ ስብራት ምክኒያት የባህር በር ሳይኖራት ቆይታለች ብለዋል።
የባህር በር ጉዳይ ለአንድ ሀገር እድገት እና ብልጽግና ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጸው ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ የባህር በር ለማግኘት የፈረመችው የመግባቢያ ስምምነት የጋራ ተጠቃሚነትን እውን የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ አክለውም ከአስራ አንድ በላይ ሀገሮች በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያሉ የባህር አካባቢዎችን እየተጠቀሙና ወታደራዊ መሰረት መገንባታቸውን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርህ በሰላማዊ መንገድ የባህር በር ለማግኘት ብሎም በጋራ ለመልማት ያሳየችው ቀናኢ ፍላጎት ሊደገፍ የሚገባ እንደሆነ ገልጸዋል።
በመድረኩ ላይ የውይይት መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት በጅማ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር እና ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ቀነኒሳ ለሚ በጽሁፋቸው የባህር በር አስፈላጊነትን አብራርተዋል።
በዚህም የባህር በር ለአንድ ሀገር የንግድ እና የኢኮኖሚ ትስስር ትልቅ ሚና አለው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የትኛውንም ሰላማዊ መንገድን ተጠቅማ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት ዘመኑን የዋጀ ስለመሆኑ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት ከኢትዮጵያም በተጨማሪ ለቀጣናው ጠቀሜታ እንዳለው የገለጹት ዶክተር ቀነኒሳ ወቅቱ ለብሔራዊ ጥቅም በአንድነት መቆም የሚያስፈልግ በመሆኑ የፖለቲካና የፍላጎት ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው ለጋራ ተጠቃሚነት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በቀጣይም በስምምነቱ ጠቀሜታ ዙሪያ ተከታታይ ውይይት በማድረግ ግንዛቤ መፍጠር የተጠናከረና የታቀደ የዲፕሎማሲ ስራ የሚያስፈልግ መሆኑን አስረድተዋል።
ሌላኛው በመድረኩ ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት ዶክተር ዳርእስከዳር ታዬ፣ በበኩላቸው ሀገራት ጥቅማቸውን የሚያጡት አልያም በሌሎች ተጽእኖ ስር የሚወድቁት የባህር በር በማጣታቸው ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ላንድ ጋር ያደረገችው ስምምነት የተሳካ የተሻለ አማራጭ መሆኑን ጠቅሰው ሂደቱ እንዲሳካ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ አስገንዝበዋል።