የትምህርት ሚኒስቴር ከኮሪያ ሪፐብሊክ ጋር በትምህርት ኢንፎርሜሽን ልውውጥና ትብብር ላይ የስምምነት ሰነድ ተፈራረመ - ኢዜአ አማርኛ
የትምህርት ሚኒስቴር ከኮሪያ ሪፐብሊክ ጋር በትምህርት ኢንፎርሜሽን ልውውጥና ትብብር ላይ የስምምነት ሰነድ ተፈራረመ
አዲስ አበባ፤ ጥር 2/2016 (ኢዜአ)፡-የትምህርት ሚኒስቴር ከደቡብ ኮሪያ ሪፐብሊክ የትምህርት ቢሮ ጊዮንግሳንግቡክ-ዶ ጋር በትምህርት ኢንፎርሜሽን ልውውጥና ትብብር ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
ስምምነቱ የትምህርት ሚንስትር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ እና የኮሪያው ጊዮንግሳንግቡክ-ዶ ቢሮ የትምህርት ዘርፍ አስተዳዳሪ ሊም ጆንግ-ሲክ መካከል ተፈርሟል።
የትብብር ስምምነቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል በ2016 እና 2017 ዓ.ም የሚደረገውን የትምህርት ኢንፎርሜሽን ልውውጥና ትብብርን የተመለከተ ነው።
ስምምነቱ በሀገራቱ መካከል ያለውን የወዳጅነትና ድጋፍ ከማጠናከሩ ባሻገር በዲጂታል የትምህርት ስትራቴጂና የማስፈጸሚያ ዕቅድ አተገባበር እንዲዳብር ለማበረታታት ያስችላል ተብሏል፡፡
በትብብር ስምምነት ሰነዱ መሰረት የኮሪያ ሪፐብሊክ መንግስት ለኢትዮጵያ የአይሲቲ መሳሪያዎችን ማቅረብና ለተመረጡ መምህራን ከትምህርታዊ መረጃ አሰጣጥ ጋር የተያያዘ ስልጠና እንደሚሰጥ ከትምህርት ሚኒስቴር ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።