የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከራሷ አልፎ ለጥቁር ሕዝቦች ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል - አቶ ደመቀ መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከራሷ አልፎ ለጥቁር ሕዝቦች ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል - አቶ ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ፤ ጥር 2/2016 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ለዘመናት ያደረገችው ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ከራሷ አልፎ ለአፍሪካውያን ብሎም ለጥቁር ሕዝቦች ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።
አቶ ደመቀ መኮንን ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በቅኝ ግዛት ዘመን ኢትዮጵያ ብቸኛዋ የጥቁር ሕዝብ ወኪል ሆና በሊግ ኦፍ ኔሽን ተሳትፋለች ብለዋል።
ይህም የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከራሷ አልፎ ለአፍሪካውያንና ለሌሎችም ጥቁር ሕዝቦች ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳበረከተች እንደሚያመለክት ገልጸዋል።
በቀደምት ዘመናት ኢትዮጵያ በልዩ ልዩ መንገድ የውጭ ግንኙነት ታካሂድ እንደነበር አቶ ደመቀ አስታውሰው፤ከ116 ዓመት በፊት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተቋቁሞ ሥራው ተቋማዊ መደረጉን አውስተዋል።
በዛሬው ዕለት የሚከፈተው ‹‹የዲፕሎማሲ ሳምንት›› ያለፉት ዓመታት የዲፕሎማሲ ጉዟችን ያሉንን ወረቶች ማየት፣ አሁን ላይ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ያሉ ዕድሎችና ፈተናዎችን መለየት የሚሉ ዓላማዎችን አንግቦ እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።
ያለፉትን ዓመታት ልምዶችና አሁናዊ ሁኔታዎችን በመገንዘብ በቀጣይነት ብሔራዊ ጥቅማችንን አስጠብቀን ለማሻገር ምን መደረግ አለበት የሚለውን ለማየት እንዲሁም የመጪው ዘመን ዲፕሎማሲን ምን መምሰል እንዳለበት የሚዳሰስበት እንደሚሆንም ጠቅሰዋል።
በዚህም ታሪክን፣ አሁናዊ ሁኔታዎችንና መጪውን ጊዜ በማስተሳሰር ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ አቅም ለመገንባት እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ሁሉም ዜጋ በዲፕሎማሲ ሥራዎች እንዲሳተፍና ጉዳዩ የሕዝብ አጀንዳ እንዲሆን ሀገራዊ ንቅናቄ ለመፍጠር የዲፕሎማሲ ሳምንት በየዓመቱ እየታሰበ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
ለውጡን ተከትሎ ብዙ ዘርፎች ላይ የሪፎርም ሥራዎች ተሠርተዋል ያሉት አቶ ደመቀ፤ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ማዕቀፍም ብሔራዊ ጥቅማችንን ማስጠበቅና ሉዓላዊነታችንን ማስከበር በሚያስችል መልኩ ሪፎርም ተደርጓል ነው ያሉት።
በዚህም የውጭ ግንኙነታችን በቀዳሚነት የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ላይ ያተኮረ እንዲሆን ሥራዎች ተሠርተዋል ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ።
በዚህም ባለብዙ ወገንና የሁለትዮሽ ወገን ላይ ያተኮረ፣ የፖለቲካ ማእቀፍ ላይ ማዕከል ያደረገ ዲፕሎማሲ እንዲሁም ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲን እንደ አንድ ትልቅ ማዕቀፍ አድርጎ የያዘ የውጭ ግንኙነት የዲፕማሲው ዋና ዋና የትኩረት መስኮች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያችን ማጠንጠኛው ከሀገራዊ ፍላጎቶችና ተጨባጭ ሁኔታዎች የሚነሳ ነው ያሉት አቶ ደመቀ፤ ቀዳሚ ዓላማውም በሁሉም መስክ ብሔራዊ ጥቅምን ማረጋገጥና ሉዓላዊነትን ማስከበር መሆኑን ገልጸዋል።
የፖሊሲ ማዕቀፉ ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ ትኩረት እንደሚሰጥ ጠቅሰው፤ ከዚህ ባለፈ ወደ አፍሪካ ብሎም ወደ ዓለም አደባባይ በባለብዙ ወገንና በሁለትዮሽ ግንኙነት እየሰፋ ይሄዳል ብለዋል።
የፖሊሲ ማእቀፉ ሲዘጋጅ ያለፉትን ዓመታት መልካም ልምዶች መነሻ በማድረግ መሆኑን ጠቅሰው በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን ተደማጭነት፣ ብሔራዊ ጥቅምና የዓለም አቀፍ ውድድርን ሀገራዊ ጥቅማችንን ባስከበረ መልኩ እውን እንዲሆን የሚያደርግ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
በኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ታሪክ በየዘመኑ ብዙ ፈተናዎች እያጋጠሙ በወቅቱ የነበሩ መሪዎችና ሕዝቡ ባደረገው ተጋድሎ ፈተናዎችን እየተሻገረች ዛሬ ላይ ደርሳለች ያሉት አቶ ደመቀ፤ በቅኝ ግዛት ዘመንም ብቸኛዋ የጥቁር ሕዝብ ወኪል ሆና በሊግ ኦፍ ኔሽን ተሳትፋለች።
ኢትዮጵያ በየዘመኑ ሲደርስባት የነበረውን ልዩ ልዩ ጫና ተቋቁማ በሠራችው ዲፕሎማሲ ከራሷ አልፎ ለአፍሪካውያንና ሌሎችም ጥቁር ሕዝቦች ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቷን ተናግረዋል።
ባለፉት ሦስት ዓመታትም በኢትዮጵያ ላይ የከፋና ዘርፈ ብዙ ጫና ሲደረግ እንደነበር አስታውሰው፤ በፀጥታው ምክር ቤት ብቻ ኢትዮጵያ ከ13 ጊዜ በላይ አጀንዳ ተደርጋ ከፍተኛ ጫና እንዲያርፍባት ተደርጓል ብለዋል።
በተጨማሪም ኢኮኖሚያዊና ልዩ ልዩ ማእቀቦች እንዲጣልባትና እርዳታንም እንደ አንድ ጫና መፍጠሪያ ለመጠቀም ተሠርቷል ነው ያሉት።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያውያን፣ መንግሥትና ወዳጅ ሀገራት ባደረጉት ከፍተኛ ርብርብና ተጋድሎ ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የሆነውን ጫና ተሻግራ ሉዓላዊነቷን፣ የግዛት አንድነቷንና ብሔራዊ ጥቅሟን አስጠብቃ መቀጠሏን አብራርተዋል።
ችግሩን ለመሻገር የኢትዮጵያን ትክክለኛ አቋም ማሳወቅ፣ በስሜት የሚመጡ ጫናዎችን ማለዘብና ወዳጅ ሀገራት የኢትዮጵያን እውነት ተገንዝበው ከጎናችን እንዲቆሙ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን አስታውሰዋል።
የዓባይ ግድብን ድርድር ከአፍሪካ አውድ ለማውጣት የተደረገውን እንቅስቃሴ በማክሸፍ ወደ አፍሪካ ማእቀፍ እንዲመለስ ማድረግ መቻሉንም ጠቅሰዋል።
በጥቅሉ በተሠራው ጠንካራ ዲፕሎማሲ ከኢትዮጵያ በተቃራኒው ቆመው የነበሩ አንዳንድ ሀገራትም የኢትዮጵያን እውነት ለመረዳት ከጎናችን ለመቆም በቅተዋል፤ በዚህ ሂደት ውስጥ ጉልህ ሚና ለነበራቸው ባለድርሻ አካላትም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማመስገናቸውንም ፕሬስ በዘገባው አስነብቧል።
በቀጣይነትም ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ያላትን ተጽእኖ ፈጣሪነት ለማስቀጠል ሀገራዊ አንድነታችንን አጠናክረን በጋራ መቆም ይጠበቅብናል ነው ያሉት።
የዲፕሎማሲ ሳምንት “ዲፕሎማሲያችን ለብሔራዊ ጥቅማችን፣ ከአፍሪካ መዲና እስከ ዓለም መድረክ” በሚል መሪ ቃል ከዛሬ ጥር 2 እስከ 24 ቀን 2016 ዓ.ም በሳይንስ ሙዚየም ይካሄዳል።