የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ የመሬት ተጠቃሚነት መብትን የሚያሰፋ ነው- ግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፤ ጥር 1/2016 (ኢዜአ)፦የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ የመሬት ተጠቃሚነት መብትን የሚያሰፋና የአርብቶ አደሩን የመሬት አያያዝና አጠቃቀም እውቅና የሚሰጥ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች እና የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተሻሻለው የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ ላይ የሕዝብና የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ አካሂዷል።


 

በግብርና ሚኒስቴር የመሬት ሕግ ባለሙያ አበባው አበበ፤ የረቂቅ አዋጁን ዓላማ፣ ይዘት፣ አስፈላጊነትና አጠቃላይ ድንጋጌዎችን በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ረቂቅ አዋጁ ለሴቶችና ድጋፍ ለሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎች በመሬት ላይ መብት የሚሰጥ፣ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ በመሬት ላይ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ፣ የአርብቶ አደሩን መብትና ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንጻር ተቃኝቶ የተዘጋጀ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በዚህም የተጠቃሚነት መብትን ማስፋት፣ የከፊል አርብቶ አደርና አርብቶ አደሩን የመሬት አያያዝና አስተዳደር ያካተተ፣ የገጠር መሬት ምዝገባና ቅየሳ ሕጋዊ ማዕቀፍ የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

አርብቶ አደሩ የሚገኝባቸው ክልሎች የአርብቶ አደር የመሬት አስተዳደር ሕግ የማውጣት ግዴታ እንዳለባቸው በረቂቅ አዋጁ መቀመጡንም ጠቅሰዋል።

የይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀትን ለብድር ዋስትና ማስያዝ፣ የገጠር መሬትና ቅየሳ፣ የገጠር መሬት የመረጃ ሥርዓት ረቂቅ አዋጅ መሠረታዊ ለውጥ ካደረገባቸው ጉዳዮች መካከል መሆኑንም ገልፀዋል።

በዚህም ማንኛውም ባለይዞታ በመሬቱ ላይ ያለውን የመጠቀም መብት በማስያዝ ከፋይናንስ ተቋማት ብድር ማግኘት ይችላል ብለዋል።

ብድሩ የሚመለስበት ጊዜና ባይመለስ የመጠቀም መብቱ አበዳሪው ለምን ያህል ጊዜ ነው የሚወስደው? የሚለውን መቀመጥ እንዳለበት ጠቁመው፤ ውል በሚደረግበት ወቅት ከአሥር ዓመት በላይ ሊሆን እንደማይገባ ተቀምጧል።

መሬት የሌላቸው ወጣቶችም ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመስማማት የቤተሰቦቻቸውን መሬት በማስያዣነት በመጠቀም ብድር የመውሰድና በተለያዩ የሥራ ዘርፎች መሰማራት እንደሚችሉ ያስቀምጣል ብለዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ የሕግ ባለሙያዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የረቂቅ አዋጁን አስፈላጊነት በማንሳት በጥንቃቄ መታየት ያለባቸው ጉዳዮች ላይ ጥያቄና አስተያየት አንስተዋል።

በረቂቅ አዋጁ የተካተተው የይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀትን ለብድር ዋስትና ማስያዝ የሚለው ድንጋጌ በጥንቃቄ መታየት ካለባቸው ጉዳዮች ውስጥ የተጠቀሰ ሲሆን ምላሽ ተሰጥቶበታል።


 

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤሊያስ፤ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ በአገሪቱ አለመኖሩ የአካባቢ መራቆትና የደን መጨፍጨፍ በማስከተሉ ወጥነት ያለው አዋጅ አስፈልጓል ብለዋል። 

ሚኒስትር ዴኤታው የተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ መብቶችን ብቻ ሳይሆን በአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ላይም ግዴታዎችን እንደሚያሰቀምጥ ጠቅሰዋል።


 

የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሰለሞን ላሌ፤ በአስረጅዎች መድረክ፣ ከባለድርሻ አካላትና ሌሎች ሃሳብ መስጫ መንገዶች ለአዋጁ ጠቃሚ ሃሳቦች መሰብሰባቸውን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም