ሀዋሳን ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ ባለሀብቶች እያደረጉት ያለው ተሳትፎ አበረታች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሀዋሳን ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ ባለሀብቶች እያደረጉት ያለው ተሳትፎ አበረታች ነው

ሀዋሳ ፤ ጥር 1/2016 (ኢዜአ)፦ ሀዋሳ ከተማን ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ የባለሀብቶች ተሳትፎ አበረታች መሆኑን የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በከተማዋ በባለሀብቶች አማካኝነት በግንባታ ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን ዛሬ ጎብኝተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ከተማዋ በብዙ መስፈርት ለኢንቨስትመንት ተመራጭና ምቹ በመሆኗ ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች መዋዕለ ንዋያቸውን ቢያፈሱ ተጠቃሚ ይሆናሉ።
ሀዋሳ ለአዲስ አበባ ባላት ቅርበትና የበርካታ ጎብኚዎችን ቀልብ የሚስቡ ሥፍራዎች ባለቤት መሆኗ ለኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዋ ወሳኝ እንደሆነም አመልክተዋል።
ሲዳማ በክልልነት ከተዋቀረበት ጊዜ አንስቶ ሀዋሳን ለኑሮና ለኢንቨስትመንት ምቹና ተመራጭ ለማድረግ የክልሉ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በዚህም በርካታ ባለሀብቶች ተስበው በተለያዩ መስኮች በመሰማራት መዋዕለ ነዋያቸውን እያፈሰሱ መሆናቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።
ባለሀብቶቹ እያካሄዱ ያሉት የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለከተማዋ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።
የክልሉ መንግሥት ባቀረቡት ፕሮጀክት መሠረት የኢንቨስትመንት ፈቃድና ቦታ ተረክበው ተግባራዊ ልማት ውሰጥ ለገቡ ባለሀብቶችን እንቅስቃሴ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ማበረታታቱን አቶ ደስታ ተናግረዋል።
በአንፃሩ መሬት ወስደው ወደ ልማት ያልገቡ አንዳንድ ባለሀብቶች ላይ ክትትል በማድረግ አስተማሪ እርምጃ መውሰዱን አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅት በከተማዋ በግንባታ ላይ ከሚገኙ ፕሮጀክቶች ውስጥ የሀዋሳ ሂልተን ሪዞርት ሆቴል፣ የሴንትራል አማረች ሪዞርትና አድማስ ሞል ሥራቸውን በተገቢው መንገድ በማከናወን ላይ እንደሚገኙ በጉብኝቱ ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።
“በሀዋሳ ያለው ኢንቨስትመንት ፍጥነቱንና ግለቱን ጠብቆ እንዲቀጥል የክልሉ መንግሥትም የከተማው አስተዳደርም የሚጠበቅብንን ለማድረግ ዝግጁ ነን” ሲሉም ተናግረዋል።
ከተማዋን የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ከሀገርም ሆነ ከውጭ ተወዳዳሪ ሊያደርጉ የሚችሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ቢመጡ ከተማዋ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኗንም ነው አቶ ደስታ ያስታወቁት።
ለዚህም የክልሉ መንግሥትና የከተማዋ አስተዳደር አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።
በ'ሰንሻይን ኮንስትራክሽን የሀዋሳ ሂልተን ሪዞርት ሆቴል ፕሮጀክት' ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢንያም ንጉሴ፣ በሀገሪቱ ታላላቅ ሆቴሎች ደረጃ የሚመደብ ሆቴል በሁለት ቢሊዮን ብር ወጪ በ30 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ እየገነቡ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ሆቴሉን በሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ግንባታውን በማጠናቀቅ ወደ ሥራ ለማስገባት መታቀዱን የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ፡ የክልሉ መንግሥትና የከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ እያደረጉላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት የሆቴሉ ፕሮጀክት ግንባታ ለ250 ሰዎች ጊዜያዊ የሥራ እድል እንደፈጠረና ግንባታው ተጠናቅቆ ወደ ሥራ ሲገባም ከ300 በላይ ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።
'የሴንትራል ቢዝነስና ቴክኖሎጂ ግሩፕ' ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ፍትህ ወልደሰንበት በበኩላቸው በ10 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ እየተገነባ ያለው ሪዞርት ግንባታ እያካሄዱ መሆኑን አስታውቀዋል።
የሀዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ መኩሪያ መርሻዬ በበኩላቸው በከተማ አስተዳደሩ በርካታ ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ፈቃድና ቦታ ተረክበው ግንባታ እያካሄዱ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ዓመት ፈቃድ የጠየቁ 250 አዲስ ፕሮጀክቶች በኢንቨስትመንት ግብረ ሃይል በመገምገም ላይ እንደሚገኙም በማመላከት።
ከዚህ ቀደም ፈቃድ ወስደውና ቦታ ተረክበው ወደ ሥራ ያልገቡ 91 ባለሀብቶች በግብረ ሃይሉ መለየታቸውንና አስተዳደራዊ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ አቶ መኩሪያ አስታውቀዋል።
በጉብኝቱ ላይ የክልሉና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራር አባላት ተሳትፈዋል።