ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሲቢኢ ኑር የሰበሰበው ተቀማጭ ገንዘብ 100 ቢሊዮን ብር መሻገሩን አስታወቀ

አዲስ አበባ፤ ጥር 1/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሲቢኢ ኑር በኩል የሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ 100 ቢሊዮን ብር መሻገሩን አስታውቋል። 

ባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት መስጠት የጀመረበትን 10ኛ ዓመት ከጥቅምት 22/2016 ዓም ጀምሮ በማክበር ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለኢዜአ በላከው መግለጫ በሲቢኢ ኑር በኩል የሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ 100 ቢሊዮን ብር መሻገሩን ገልጿል። 

ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በመስጠት ፈር ቀዳጅ መሆኑን የጠቀሰው ባንኩ፤ በባንክ ኢንዱስትሪ ታሪክ በአጭር ጊዜ 100 ቢሊዮን ተቀማጭ መሰብሰብ የቻለ ባንክ ስለመሆኑም ነው የገለጸው።

በዚህም በባንክ ኢንደስትሪ ታሪክ በአጭር ጊዜ 100 ቢሊየን ብር ተቀማጭ መሰብሰብ የቻለ ባንክ መሆኑንም በመግለጫው ተመላክቷል።

ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎቱ የሸሪዓ መርህን መሰረት በማድረግ የሚሰጥ ሲሆን ከህብረተሰቡ ዕሴት እና ፍላጎት ጋር ተጣጥሞ ሲሰራበት ከፋይናንስ ተደራሽነትና አካታችነት ባለፈ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑንም ገልጿል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት መንግስት በፋይናንስ ዘርፉ ላይ የወሰዳቸው ጠንካራ የማሻሻያ እርምጃዎችን ተከትሎ ባንኩ ያደረጋቸው የመዋቅር፣ የአሰራር እና የአገልግሎት አሰጣጥ ለውጦች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ህብረተሰብ በከፍተኛ ደረጃ ወደ ባንከ አንዲመጣና የተሟላ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ተችሏል ብሏል ባንኩ በመግለጫው። 

ባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በሰጠባቸው ባለፉት 10 ዓመታት፤ ከ40 በላይ በሚሆኑ የወዲዓህ መርህ መሰረት ያደረጉ የአደራ እና የተንቀሰቃሽ እንዲሁም ትርፍ አጋሪ በሆነው በሙዳራባህ መርህን መሰረት ያደረጉ የተቀማጭ ሒሳቦችን መሰረት በማድረግ 6.6 ሚሊዮን ደንበኞችን በማፍራት ከ100 ቢሊዮን ተቀማጭ ገንዘብ በላይ ማሰባሰብ መቻሉን ጠቁሟል። 

በአሁኑ ጊዜ የሲቢኢ ኑር የባንክ አገልግሎት በ1ሺህ 934 ቅርንጫፎች እየተሰጠ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከልም 153 ሙሉ በሙሉ አገልግሎቱን ብቻ የሚሰጡ ቅርንጫፎች ስለመሆናቸውም ከባንኩ ተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ባንኩ አክሎም በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት ባንኩ እየሰጠ ላለው ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት የተለየ ትኩረት በመስጠት ያከናወናቸው ተግባራት አሁን ላይ ለሚታዩት ለውጦች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አስታውቋል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም