ወደብን ጨምሮ በውሃ አካላት ላይ የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ወደብን ጨምሮ በውሃ አካላት ላይ የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 1/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ወደብን ጨምሮ በውሃ አካላት ላይ የማሪን ቴክኖሎጂን በመጠቀም የአየር ትንበያ አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ ከኢትዮጵያ አልፎ ጎረቤት አገራትን ተጠቃሚ የሚያደርግ የሚቲዮሮሎጂ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አቅም እንዳለውም ገልጿል።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ የአየር ትንበያ አገልግሎት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
የአየር ትንበያ አገልግሎት ለአቪየሽን ዘርፉ የጀርባ አጥንት ሆኖ እያገለገለ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚያው ልክ የውሃ ትራንስፖርትም አገልግሎቱን ሊጠቀም እንደሚገባ አመልክተዋል።
ኢንስቲትዮቱ ወደብን ጨምሮ በውሃ አካላት ላይ የውሃ ትራንስፖርትን ማሳለጥ የሚችል የማሪን ቴክኖሎጂን በመጠቀም የአየር ትንበያ አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን ዝግጅት እያደረገ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት የባህር በር የሌላት ሆና በመቆየቷ ቴክኖሎጂውን ወደ ስራ ማስገባት አለመቻሏን አስታውሰው፣ በተለይም በቅርቡ ከሶማሌላንድ ጋር የባህር በር ለማግኘት የተደረገው ስምምነት ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም ምቹ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።
ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ከኢትዮጵያ አልፎ ጎረቤት አገራትን ተጠቃሚ የሚያደርግ የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አቅም መኖሩንም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት አባልና የአፍሪካ ሊቀመንበር እንደመሆኗ ዓለም አቀፍ የአየር ትንበያ ልውውጦችን በማድረግ ተዓማኒነት ያለው መረጃ መስጠት የሚያስችላት አቅም እንዳለ ገልጸዋል።
በዚህም በውሃ አካላት ላይ የሚቲዎሮሎጂ መረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያዎችን በመትከል አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የአየር ትንበያ መረጃ አሰባሰብ ሰርዓቱን የበለጠ ዘመናዊ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።
ለአብነትም በውሃ አካላት ላይ የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ለመስጠት የሚደረገውን ዝግጅት ጨምሮ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላኖች ላይ የአየር ሁኔታ መረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያዎች ለመግጠም እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ትንበያ አገልግሎትን ተደራሽና ተዓማኒ ለማድረግ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት(ኢጋድ)ን ጨምሮ ከዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅትና ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በጋራ እየሰራች ነው ብለዋል።