የማርን ጥራት ፣  ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው

አዳማ ፤ ጥር 1 / 2016(ኢዜአ)፡- በሀገሪቱ የማርን ጥራት ፣ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ  እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ። 

በማር ምርትና ምርታማነት ተግዳሮቶች፣ በምርቱ ጥራትና የውጭ ግብይት ዙሪያ የተካሄደ ጥናትን  ለመተግበር የሚያስችል ግብዓት ለማግኘትና ለማዳበር ያለመና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የንቅናቄ መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።

በዚህ ወቅት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሣ  ለኢዜአ እንደገለፁት፤  በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብሩ የማር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ በርካታ የማር ማምረቻ መንደሮች ተደራጅተዋል።

 ለአርሶ አደሩ የንብ ማነብ የክህሎት ስልጠና መስጠት፣ ወጣቶችን በስፋት አደራጅቶ በዘርፉ ወደ ስራ ማስገባት እንዲሁም ሻጭና ገዥን የማገናኘት ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።

የተካሄደው ጥናትም  የማር ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ ጥራት ያለው የማር ምርት በዓይነትና በመጠን በማምረት ወደ ውጭ ለመላክ የሚያስችል መሆኑንም  ገልጸዋል።

የማር ምርት በዘንድሮው ዓመት በአውሮፓ ገበያ  እውቅና የተገኘ ቢሆንም አሁንም የማር ምርት ጥራት ችግር ያለበት መሆኑንና በቀጣይ በትኩረት የሚሰራበት መሆኑንም ዶክተር ሶፊያ አመልክተዋል።


 

የኢትዮጵያ እንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አስራት ጤራ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ የማር ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በአቅም ግንባታና ክህሎት ስልጠና እንዲሁም በዘርፉ የጥናትና ምርምር ስራ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም የማር ምርቱ ገበያ ተኮር ሆኖ እንዲመረት ኢንስቲትዩቱ የክህሎት ስልጠናና የማማከር ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዚህም የማር ምርቱ በጥራትና በስፋት እንዲመረት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ የግብርና መዋቅሩ ባጠቃላይ በግብዓት አቅርቦት ፣የዕውቀትና ክህሎት ስልጠና መስጠት ላይ በቅንጅት መስራት ይጠብቅብናል ብለዋል።


 

በኢንስቲትዩቱ የማርና ሰም ተመራማሪ ዶክተር አውራሪስ ጌታቸው ባቀረቡት የጥናት ግኝት በአገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የማር ማምረት አቅም ቢኖርም በምርቱ ላይ የጥራት መጓደል እንዲሁም በበቂ ሁኔታና በሚፈለገው መልኩ ያለማምረት ችግር አለ ብለዋል።

በተለይም ምርትና ምርታማነት ላይ ካሉት ችግሮች መካከል የንብ ማነብ ስራ በስፋት ባህላዊ መሆኑ፣ የምርት መጠኑ ዝቅተኛነት፣  የክህሎት ክፍተት፣ የንብ መንጋ ንግድ  ያለመኖርና የአበባ ወቅቶች ያለመገንዘብ ዋና ዋናዎቹ ናቸው ብለዋል።

በተጨማሪም የማር ጥራት በተለይም ማር ሳይበስል መቁረጥ፣ የማከማቻ ቦታ የጥራት ጉድለትና የማር ምርት አካባቢ የፅዳት ጉድለት ሌላኛው በጥናቱ የተለዩ ችግሮች ናቸው ብለዋል።

በተመሳሳይ የሀገር ውስጥ የማር ምርት ዋጋ ከፍተኛ መሆንና አቅርቦቱና ፍላጎቱ ያለመጣጣም የማር የወጪ ንግድ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠሩን ጠቅሰው ችግሩን ለመቅረፍ የተትረፈረፈ የማር ምርት እንዲኖር የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብሩን ለማሳካት መረባረብ እንደሚገባ አመልክተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም