ቀጥታ፡

የወንጀል ድርጊቶችን ዜጎች ካሉበት ሆነው ለፖሊስ የሚያደርሱበት የሞባይል መተግበሪያ በቅርቡ በአዲስ አበባ  ሥራ ሊጀምር ነው 

አዲስ አበባ፤ ጥር 1/2016(ኢዜአ)፡- የወንጀል ድርጊቶችን ዜጎች ካሉበት ሆነው ለፖሊስ የሚያደርሱበት የሞባይል መተግበሪያ በቅርቡ በአዲስ አበባ ሥራ የሚጀምር መሆኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከለውጡ በኋላ የሀገርንና የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት በማስጠበቅ ረገድ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዙ በርካታ የለውጥ ሥራዎችን አከናውኗል።

የሰው ኃይል እና የቴክኖሎጂ አቅሙን በማሳደግ የሕዝብና መንግሥትን ኃላፊነት በላቀ ብቃት በመወጣትም ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፤ ፖሊስ በቴክኖሎጂ በመታገዝ እንዲሁም ከኅብረተሰቡ ጋር በሚያከናውናቸው የጸጥታና ደኅንነት ሥራዎች የሰላም ማስጠበቅ ሥራ በስፋት እየተከናወነ ነው ብለዋል።

ፌደራል ፖሊስ የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት የማስጠበቅ ተልዕኮውን በብቃት ለመወጣት የሰው ኃይል አቅሙን ከቴክኖሎጂ ጋር በማስተሳሰር እየሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

በዚህም በአፍሪካ እስካሁን ያልተሞከረ በዓለም ላይም እምብዛም ያልተለመደ የዜጎችን የጸጥታ ሥራ የሚያግዝ በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች የበለፀገ ዘመናዊ የሞባይል መተግበሪያ ሥራ ላይ ይውላል ብለዋል።

የሞባይል መተግበሪያው ዜጎች ባሉበት ቦታ ሆነው የወንጀል ድርጊቶችን ለፖሊስ ማድረስ የሚያስችል ቴክኖሎጂ መሆኑን ጠቁመው፤ በቅርቡ በአዲስ አበባ ሥራ ይጀምራል ብለዋል፡፡

መተግበሪያው ዜጎች በእጅ ስልካቸው ለፖሊስ መረጃ የሚያደርሱበትና በወንጀል መከላከል ሥራ የፖሊስና ሕብረተሰቡን ትብብር ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገልፀዋል። 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም