ሁለተኛው ትውልድ ማህበረሰብ አባላት ድሬዳዋ መግባት ጀመሩ - ኢዜአ አማርኛ
ሁለተኛው ትውልድ ማህበረሰብ አባላት ድሬዳዋ መግባት ጀመሩ
ድሬዳዋ ፤ ጥር 1/ 2016(ኢዜአ)፡- በመላው ዓለም የሚገኙ የሁለተኛው ትውልድ ማህበረሰብ አባላት ወደ ድሬዳዋ መግባት መጀመራቸው ተገለጸ።
በውጭ የሚኖሩ የድሬዳዋ ተወላጆች በከተማ አስተዳደሩ በኢንቨስትመንት በመሰማራት የሥራ ዕድል መፍጠራቸው ተመልክቷል።
የድሬደዋ አስተዳደር የባህልና ቱሪዝምና የድሬዳዋ የዲያስፖራ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቶች መግለጫ ሰጥተዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሚካኤል እንዳለ እንዳስታወቁት፤ ከ150 በላይ የሚሆኑ የድሬዳዋ ተወላጅ የሆኑ የሁለተኛው ትውልድ ማህበረሰብ አባላት ወደ ከተማዋ እየገቡ ነው።
እስካሁንም 30 የሁለተኛው ትውልድ አባላት ድሬዳዋ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ አቀባበል እንደተደረገላቸው ገልጸዋል።
የሁለተኛው ትውልድ አባላት በቆይታቸው በከተማዋ የሚገኙ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ የቱሪስት መዳረሻዎች በመጎብኘት ታሪክና ባህሉን እንዲያውቁ ይደረጋል ብለዋል።
በተጨማሪም በአስተዳደሩ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን እንደሚጎበኙ ኃላፊው ተናግረዋል። `
በተጨማሪም በኢንቨስትመንት ዘርፍ ተሰማርተው ዕውቀታቸውን፣ ሃብታቸውንና የቴክኖሎጂ ክህሎታቸውን ስራ ላይ እንዲያውሉ ጥረት ይደረጋል ብለዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር የዳያስፖራ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢንያም ግርማ በበኩላቸው፤ በመላው ዓለም የሚገኙ የድሬዳዋ ተወላጆች በጤና፣ በትምህርትና በማህበራዊ ልማት መስኮች በገንዘብና በዕውቀት ተሳትፎ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።
በተጨማሪም በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በጤናና በሆቴል ኢንቨስትመንት ዘርፎች በመሰማራት ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውንም ተናግረዋል።
"በየዓመቱ ለቤተሰብና ዘመድ የሚልኩትየውጪ ምንዛሬ እየጨመረና ለአገር ሁለንተናዊ ዕድገት የድርሻውን እያበረከተ ይገኛል፤ ባለፈው ዓመት ብቻ በተለያዩ ባንኮች ለቤተሰቦቻቸው 64 ሚሊዮን ዶላር ልከዋል" ብለዋል።
ወደ ድሬዳዋ እየገቡ የሚገኙት የሁለተኛው ትውልድ አባላት የኢትዮጵያ ታላቅነትና ታሪክ ከመረዳትና ከማወቅ ባለፈ፤እንደ ወላጆቻቸው በአገር ሁለንተናዊ የለውጥና የዕድገት ጉዞ ሚና ይጫወታሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የሁለተኛው ትውልድ አባላት የወላጆቻቸውን አገር እንዲጎበኙ ጥሪ ያደረጉ ሲሆን፤ በመጀመሪያው ዙር ወደ ኢትዮጵያ መግባት ጀምረዋል።