በአማራ ክልል የዘንድሮው የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የዘንድሮው የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራ ተጀመረ

ደሴ ፤ጥር 1/2016(ኢዜአ)፦የአማራ ክልል በተያዘው በጋ ወራት በ376 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚከናወነውን የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራ በደቡብ ወሎ ዞን ተሁለደሬ ወረዳ ዛሬ ተጀምሯል።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዱ ሁሴንን ጨምሮ ሌሎች የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በዚሁ ጊዜ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ድረስ ሳህሉ፣ የዘንድሮው የበጋ ወራት የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ በልዩ ትኩረት ይከናወናል ብለዋል።
የተፈጥሮ ሃብት ልማቱ ለክልሉ ሁለንተናዊ እድገት ያለውን ጠቀሜታ በመረዳት የተራቆተና ገደላማ አካባቢዎችን በማልማት ዘላቂ ጠቀሜታ እንዲሰጡ በሚያስችል አግባብ እንደሚከናወን ተናግረዋል።
የልማት ስራውን በተመረጡ 9 ሺህ 60 ተፋሰሶች፣ በ376 ሺህ በሚበልጥ መሬት ላይ ለማከናወን ቅደመ ዝግጅት በማጠናቀቅ ዛሬ በይፋ መጀመሩን ገልጸዋል።
ለዚህም ለቀያሽ አርሶ አደሮችና ባለሙያዎች በየደረጃው ስልጠና መሰጠቱንና የልማት መሳሪያዎችም ልየታ መከናወኑን ተናግረዋል።
ቀደም ሲል በተሰሩ የተፈጥሮ ሀብት ስራዎች ተጨባጭ ውጤት መገኘቱን ጠቁመው፤ ይህነኑ ለማስቀጠልም የዚህ ዓመት የልማት ስራ በተሻለ ጥራትና ፍጥነት እንዲከናወን ይደረጋል ብለዋል።
በተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራውም ከ4 ሚሊዮን በላይ ሰው በተደራጀ አግባብ የሚሳተፍ እንደሆነም አብራርተዋል።
''ለዞናችን የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ህብረተሰቡን በማስተባበር ስራው ተጀምሯል'' ያሉት ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ መኮንን ናቸው።
በዘንድሮው የበጋ ወራትም ከአንድ ሺህ በሚበልጡ ተፋሰሶች ላይ በማልማትና በቀጣይ ክረምት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች ጭምር በመትክል ለስራ እድል መፍጠሪያነት እንዲውሉ ይሰራል ብለዋል።
በተሁለደሬ ወረዳ የ08 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አህመድ ዳውድ እንዳሉት፤ ባለፉት ዓመታት በሰሯቸው የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራዎች የሚታይ ለውጥ ተገኝቷል።
በዚህም ለእንስሳት መኖ ምንጭ እንደሆናቸው ጠቅሰው፤ የአፈር ለምነት በመጠበቁም የሰብል ምርታማነት ማደጉን ገልፀዋል።
''በራሳችን ተነሳሽነት ለአንድ ወር ያህል እርከን፣ ክትርና ሌሎችንም በማከናወን የአካባቢያችንን መልካም ምድር እንጠብቃለን'' ብለዋል።
የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መሃመድ ሰይድ፣ ''ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጠቀሜታው በተግባር በማየታችን በየዓመቱ በራሳችን ተነሳሽነት በመስራት የማሳችንን የአፈር ለምነት መጠበቅ ችለናል'' ብለዋል።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ የክልል፣ የምስራቅ አማራ ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።