በትግራይ ክልል የአየር ንብረት ለውጥንና ድርቅን ለመከላከል 382 ተፋሰሶች የሚለሙበት ፕሮጀክት እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል የአየር ንብረት ለውጥንና ድርቅን ለመከላከል 382 ተፋሰሶች የሚለሙበት ፕሮጀክት እየተካሄደ ነው
መቐሌ፤ ጥር 1/2016(ኢዜአ)፦ በትግራይ ክልል የአየር ንብረት ለውጥንና ድርቅን ለመከላከል 382 ተፋሰሶች የሚለሙበት ፕሮጀክት እየተካሄደ መሆኑን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ አስታወቀ።
ፕሮጀክቱ ለሚቀጥሉት ስድስት ዓመታት የሚቆይ ሲሆን፣ በዓለም ባንክና በፌዴራል መንግሥት ድጋፍ እንደሚካሄድ ተገልጿል።
በቢሮው የልማት ተፋሰስ ፕሮጀክት ትግበራ አስተባባሪ አቶ ይትባረክ ገብረመድህን ለኢዜአ እንዳሉት፤ በክልሉ በተመረጡ ወረዳዎችና አካባቢዎች በ382 ተፋሰሶች ላይ የተቀናጀ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራዎች ይከናወናሉ።
ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ በተያዘው በጀት ዓመት ዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር በጀት እንደተመደበለትም አስታውቀዋል።
በፕሮጀክቱ 64ሺህ አባወራዎችን ያቀፉ 382 የተፋሰስ ልማት ኅብረት ሥራ ማህበራት ተደራጅተው ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል።
በክልሉ በ300 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ካለፈው ወር ጀምሮ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንና በቀጣይ ክረምት በዚሁ መሬት ላይ የችግኝ ተከላ እንደሚካሄድ አቶ ይትባረክ ገልጸዋል።
በፕሮጀክቱ የሚሳተፉ የኅብረት ሥራ ማህበራት አባላት በቀን ክፍያ እንደሚያገኙ ገልጸው፣ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የራሳቸውን የልማት ሥራዎች በማካሄድ ተጠቃሚዎች እንደሚሆኑ አስረድተዋል።
በተፋሰሶቹ የሚካሄደው ልማት የአካባቢውን የአየር ንብረት ሚዛን ከመጠበቅ በተጨማሪ፣ አርሶ አደሮች በንብ ርባታ፣ በእንስሳት መኖና በመስኖ ልማት ሥራዎች በመሳተፍ ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ለሚቀጥሉት ስድስት ዓመታት እንደሚቆይ አስተባባሪው ጠቅሰው፤ በዓለም ባንክና በፌዴራል መንግሥት ድጋፍ እንደሚከናወን አስታውቀዋል።
በእንደርታ ወረዳ የዓራቶ ገጠር ቀበሌ አርሶ አደር ፍሰሃ መኮንን በሰጡት አስተያየት፤ በፕሮጀክቱ በሚያደርጉት ተሳትፎ መጠን ክፍያ በማግኘት ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውንና የአካባቢውን የተፈጥሮ ሀብት ልማት ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲደርስ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
''በመልማት ላይ የሚገኙ ተፋሰሶች በሰው ሰራሽና ተፈጥሮ አደጋ ጉዳት እንዳይደርስበት እየተከላከልን በንብ ርባታና በእንስሳት ሃብት ልማት ለመጠቀም ዝግጁ ነን'' ያሉት ደግሞ የዚሁ ቀበሌ አርሶ አደር ሐዱሽ ገብረየሱስ ናቸው።