በአምስት ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረበ የአበባ ምርት ከ184 ነጥብ 7 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ - ኢዜአ አማርኛ
በአምስት ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረበ የአበባ ምርት ከ184 ነጥብ 7 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ
አዲስ አበባ፤ ጥር 1/2016(ኢዜአ)፦ በበጀት ዓመቱ አምስት ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረበ የአበባ ምርት ከ184 ነጥብ 7 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።
የአበባ ልማት፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ እጸ ጣዕም፣ ሥራሥር፣ እንሰት፣ ቡና፣ የሻይቅጠልና ቅመማቅመም ምርቶች በሆርቲካልቸር ዘርፍ የሚካተቱ ምርቶች ናቸው።
በኢትዮጵያ እነዚህ ምርቶች ለውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ለሥራ ዕድል፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓትና ሌሎችም ጥቅሞች እየዋሉ ይገኛሉ።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው በግብርና ሚኒስቴር የሆርቲካልቸር ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አብደላ ነጋሽ፤ በተለይም በአበባ ልማት ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ከዘርፉ ለማግኘት ከታቀደው ጥቅምና የውጭ ምንዛሬ ግኝት አንፃር ግን አሁንም ዝቅተኛ ስለመሆኑ ያነሳሉ።
በበጀት ዓመቱ አምስት ወራት ወደ ውጭ ለመላክ ከታቀደው 55 ሺህ 852 ቶን የአበባ ምርት ማሳካት የተቻለው 38 ሺህ 949 ቶን ወይም የዕቅዱን ከ70 በመቶ በታች መሆኑን ጠቅሰዋል።
የተገኘው ገቢም ከ184 ነጥብ 7 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ቢሆንም ከአምናው ተመሳሳይ ወራት ጋር ሲነጻጸር የ30 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን ገልፀዋል።
የመሠረተ-ልማት አለመሟላት፣ የቅንጅት መጓደልና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች የዘርፉ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይ የተሻለ ስኬት ለማስመዝገብ ከፍተኛ ጥረት ይደረጋል ብለዋል።
በአበባ ልማት ላይ በአንዳንዶች ዘንድ የተሳሳተ ግንዛቤ መኖሩን ጠቁመው ጉዳዩን በግልጽ ማስረዳትና ማሳወቅ እንዲሁም ቅንጅታዊ ሥራዎችን ማጠናከር ተገቢ መሆኑን አመልክተዋል።
በዘርፉ ልማት ጥቅም ላይ የሚውሉ ኬሚካሎች በዓለም ላይ የተፈቀዱና ሥራ ላይ የሚውሉ በመሆናቸው ለሰውም ይሁን ለእንስሳት ጉዳት የሌላቸውና ከአካባቢ ብክለትም ነፃ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ለአበባ ልማት የሚውል የመሬት አቅርቦት ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ አብደላ ለሊዝ አልሚዎች የውል ማቋረጥና ተያያዥ ችግሮች በዘላቂነት ሊፈቱ ይገባል ነው ያሉት።
በዘርፉ በስፋት ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው አልሚዎች ተጨማሪ መሬት የሚያገኙበትን አሠራር መዘርጋት ያስፈልጋል ብለዋል።