የኢትዮጵያ የገለልተኝነት፣ ለጋራ ጥቅምና መፍትሔ የመሥራት የዲፕሎማሲ አቋም ከጥንት እስካሁንም የዘለቀ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የገለልተኝነት፣ ለጋራ ጥቅምና መፍትሔ የመሥራት የዲፕሎማሲ አቋም ከጥንት እስካሁንም የዘለቀ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 1/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የገለልተኝነት፣ ለጋራ ጥቅምና መፍትሔ የመሥራት የዲፕሎማሲ አቋም ከጥንት እስካሁንም የዘለቀ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር አንተነህ ጌታቸው ገለጹ።
በ1900 ዓ.ም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተቋቁሞ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ተቋማዊ አሠራር ቢጀመርም የዲፕሎማሲ ግንኙነት ታሪኳ ግን ከዚህም የቀደመ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በመንግሥታት ልዩነት የትኩረት ለውጦች ሊኖሩት ቢችሉም ለማንም አካል ያልወገነ፣ የጋራ ልማትና ተጠቃሚነትን መሠረት በማድረግ እስካሁንም የዘለቀ መሆኑ ይታወቃል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር አንተነህ ጌታቸው፤ በዓለም የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ውስጥ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ፍትሃዊና ገለልተኝነትን በማንገብ ዘመናትን የተሻገረ ስለመሆኑ ያብራራሉ።
በዛግዌ ስርወ-መንግሥት ወቅት የአውሮፓ ክርስቲያኖች መካከለኛው ምስራቅ ካሉ አረቦች ባደረጉት የመስቀል ጦርነት “ኢትዮጵያ የክርስቲያን መንግሥት ነች፤ ከጎናችን ልትቆም ይገባል” በሚል አውሮፓውያን ጥሪ ባቀረቡበት ወቅት በጊዜው የነበሩት ንጉስ ገለልተኛ አቋም ማራመዳቸውን ለአብነት ይጠቅሳሉ።
"የኢትዮጵያ የሁልጊዜ ውግንና ከብሔራዊ ጥቅሟ ጋር ነው" የሚሉት ተመራማሪው የገለልተኝነት አካሄድ ለጋራ ጥቅምና መፍትሔ የመሥራት የዲፕሎማሲ አቋሟ ከጥንት እስካሁንም የዘለቀ ነው ይላሉ።
በቅርቡ ብሪክስን መቀላቀሏም ብሔራዊ ፍላጎቷን የማስጠበቅና በጋራ የመልማት መርህን መሠረት ያደረገ የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ሥራ አካል መሆኑን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ የባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ፖሊሲዋ በመስኩ የምትታወቅበትና በጉልህ የምትጠቀስበት መሆኑን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1919 የሊግ ኦፍ ኔሽን ይህን የመጀመሪያ የዓለም አቀፍ የበይነ- መንግሥታት ተቋም በመተካት በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1945 የተቋቋመው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዲሁም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 1963 የተቋቋመው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ የአፍሪካ ሕብረት) መሥራች አገር ናት።
በባለብዙ ወገን ተቋማቱም ከራሷ ጥቅም ባለፈ የጥቁር ሕዝቦችንና የአፍሪካውያን በተለይም በቅኝ ግዛት ሥር የነበሩ አገራትን ድምፅ በማስተጋባት የምትታወቅ መሆኑን ነው ዶክተር አንተነህ የሚገልጹት።
በሊግ ኦፍ ኔሽን የማቋቋሚያ ቻርተር ከነበሩ ቁልፍ ጉዳዮች መካከል የጋራ ደኅንነት የሚለው አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ በወቅቱ ኃያላን አገራት በታዳጊ አገራት ላይ የሚያሳድሩትን ተፅዕኖ በመቃወም ድምፅ መሆኗንም አስታውሰዋል።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1936 አፄ ኃይለሥላሴ በሊግ ኦፍ ኔሽን ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በጣልያን ተወራ ተቋሙ አለመደገፉን በማንሳት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መመስረት አስተዋፅዖ እንዳበረከቱ አንስተዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ በዘመናት መካከል በራሷ ችግር ውስጥም ሆና በቻለችው አቅም ሁሉ በዓለም የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ የማይጠፋ አሻራ ማኖሯን ገልፀዋል።
በተለያዩ የዲፕሎማሲ ጥረቶች እንዲሁም በአየር ንብረት ለውጥ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የአፍሪካ ወካይ ድምፅ ሆና መቀጠሏን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ አካሄዷ የጋራ ፍላጎትን በጋራ የማሳካት ለጋራ ችግሮች የጋራ መፍትሔ በሚሉት ዐብይ ጽንሰ-ሀሳቦች የተመሠረተ መሆኑን ነው ተመራማሪው ያነሱት።
የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ድንገት በቀልና ትናንት የተከሰተ አይደለም ያሉት ዶክተር አንተነህ፤ ዲፕሎማሲው የትናንት መነሻ እርሾ ያለው የጋራ መተላለፊያ መንገድ ሆኖ ያገለገለና የነገውን የተሳሰረ ዕጣ ፈንታ በውስጡ የያዘ መሆኑን ገልፀዋል።
የአጀንዳ በየጊዜው መቀያየር፣ መብዛትና የዲጂታላይዜሽን መስፋፋት አሁን ላይ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴው ፈተና መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ዘመኑን በዋጀ መልኩ በሰጥቶ መቀበል መርህ ስትራቴጂካዊ አቅሞችን ለዓለም ማሳየት ይጠበቅባታል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለቀጣናው፣ ለአፍሪካና ዓለም ሰላም መጠበቅ እንዲሁም ለጋራ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ያላትን መሻት ይበልጥ በዲፕሎማሲው አማራጮች ማስተዋወቅ ይገባታልም ነው ያሉት።
በተለይም ከአገራዊ ለውጡ በኋላ ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገራት ጋር የፈጠረችውን ስትራቴጂክ አጋርነት ይበልጥ ማስፋትና አጠናክራ መቀጠል ይኖርባታል ሲሉ ተናግረዋል።