የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዘመናዊ የቤት አስተዳደር ሥርዓትን ለመፍጠር የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ መቀጠል አለበት - ኢዜአ አማርኛ
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዘመናዊ የቤት አስተዳደር ሥርዓትን ለመፍጠር የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ መቀጠል አለበት

አዲስ አበባ፤ ጥር 1 /2016 (ኢዜአ)፦ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የጀመረውን ዘመናዊ የፋይናንስ ሥርዓት ዝርጋታ ፣ አዳዲስ የግንባታ ቴክኖሎጂ ማስፋት፣ ዘመናዊ የቤት አስተዳደር ሥርዓት ከመፍጠር አኳያ እና የጀመራቸውን ገቢ የሚያሳድጉ ተግባራት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ አሳሰበ።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አብዱረማን ኢድ ጣሂርን ጨምሮ ሌሎች የማኔጀመንት አባላት የኮርፖሬሽኑን የተቋም ግንባታ ሪፎርም አፈጻጸም ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡
ከፍተኛ አመራሮቹ በዋናው መስሪያ ቤት ቢሮዎችና በቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ፣በመጠናቀቅ ላይ ባለው በገላን ባቺንግ ፕላንት፣ ለአገልግሎት በበቁት በመካኒሳና ቀበና ሳይቶች እና በመጠናቀቅ ላይ ባለው በኮከበ ጽባህ ሳይት ጉብኝት አድርገዋል፡፡
በጉብኝታቸውም በግንባታው ዘርፍ አቅርቦትን የሚያሳልጥ የኮንክሪት ሚክስና የብሎኬት ማምረቻ ማሽን ተከላ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን መመልከታቸውን አመራሮቹ ገልጸው፤ይህም የኮንስትራክሽን ዘርፉን በማሰደግ ረገድም ኮርፖሬሽኑ የድርሻውን ለመወጣት እንደሚያስችለው ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብዱረማን ኢድ ጣሂር እንደገለጹት ኮርፖሬሽኑ ከነበረበት ውስብስብ ችግር ታላቆ አሁን ለደረሰበት ስኬትና ውጤት አድናቆት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
ተቋሙ ለበርካታ ዓመታት በይደር የተከማቹ የሂሳብ ሪፖርቶችን በካሔደው ሪፎርም አስተያየት መስጠት ከማይችልበት የኦዲት አስተያያት ወደ አዎንታዊ የኦዲት አስተያየት እንዲያስመዘግብ መደረጉና ለንጹሁ ኦዲት አስተያየያት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በዚህም፤ የጀመረውን ዘመናዊ የፋይናንስ ሥርዓት ዝርጋታ ፣ አዳዲስ የግንባታ ቴክኖሎጂ ማስፋት ፣ ዘመናዊ የቤት አስተዳደር ሥርዓት ከመፍጠር አኳያ እና የጀመራቸውን ገቢ የሚያሳድጉ ተግባራት አጠናክሮ እንዲቀጥል ዋና ሥራ አስፈጻሚው አሳስበዋል።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ ከማል ከአመራሮቹ ለቀረቡት አስተያየቶች በሰጡት ምላሽ በተለይ የቤት ልማት ፋይናንስ ማፈላለግ ረገድ ኮርፖሬሽኑ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ድጋፍ እንደሚፈልግ ገልጸዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ በዋናነት ዘመናዊ ግንባታ ቴክኖሎጂን ለማስፋት የገቢ አቅም ለማሳደግ የሚያችሉ የጀመራቸውን በርካታ ተግባራት አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል አቶ ረሻድ አረጋግጠዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የተሠጡትን ገንቢ አስተያየቶችን ወስዶ እንደሚሰራም የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተናግረዋል፡፡