የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሸኛኘት ተደረገለት - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሸኛኘት ተደረገለት
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 30/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሸኛኘት ተደርጎለታል።
በኮሎምቢያ ለሚካሄደው የ2024ቱ የሴቶች ከ20 አመት በታች አለም ዋንጫ ለመካፈል የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የመጨረሻ ጨዋታውን ከሞሮኮ ጋር ያደርጋል።
ቡድኑ በአዲስ አበባ ስታድየም የመጨረሻ ልምምዱን ዛሬ የሰራ ሲሆን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አማካኝነት ለልኡካን ቡድኑ በስካይ ላይት ሆቴል አሸኛኘት ተደርጎላቸዋል።
በሽኝት ፕሮግራሙ ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ባህሩ ጥላሁንና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ተገኝተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ቡድኑ ጠንካራ ዝግጅት እንዳደረገ መመልከታቸውን በመጥቀስ ለቡድኑ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
ብሔራዊ ቡድኑ የመልሱን ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም እንዲጫወት አስፈላጊው ሁሉ ጥረት እንደሚደረግ በመግለጽ ለብሄራዊ ቡድኑ መልካም እድል በመመኘት የሰንደቅ አላማ ርክክብ ማድረጋቸውን ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጃራ በበኩላቸው ብሔራዊ ቡድኑ ሞሮኮ ላይ የሚያደርገውን ጨዋታ በውጤት በማጠናቀቅ ኮሎምቢያ በሚካሔደው ከ20 ዓመት በታች ተሳታፊ ለመሆን ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለበት ብለዋል።