ቀጥታ፡

ወደ 4 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል-የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን

አዲስ አበባ፤ ጥር 1 /2016(ኢዜአ)፦ ወደ 4 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የኢፌዴሪ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽንና በተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለውን ወቅታዊ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት በተመለከተ የጋራ መግለጫ አውጥተዋል።

በመግለጫውም የኢትዮጵያ መንግስት ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የግብርና ምርታማነትን በማሳደግና የምግብ ዋስትና መረጋገጥ ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑ ተገልጿል።

ይሁን እንጂ በተደጋጋሚ እየተከሰተ የሚገኘው ድርቅ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመከላከል የሁሉንም አጋር አካላት ድጋፍና ትብብር እንደሚጠይቅ በመግለጫው ተመላክቷል።

መግለጫው አክሎም በአፋር፣ አማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያ ፣ደቡብ ፣ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች በድርቅ በተጠቁ አካባቢዎች ወደ 4 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው አስታውቋል።

ድርቁን ተከትሎ ካጋጠመው የምግብ እጥረት ባለፈ በነዚህ አካባቢዎች እንደ ወባ፣ ኩፍኝና ኮሌራ ያሉ በሽታዎች መከሰትን ጨምሮ በቀንድ ከብቶች ላይም ጉዳት እየደረሰ መሆኑ ተገልጿል።

ያለው ስር የሰደደ የሃብት ውስንነት እንዳለ ሆኖ ድጋፎቹን በሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች ለማዳረስ በአንዳንድ ኪስ አካባቢዎች የሚያጋጥመው የጸጥታ ችግር የሰብዓዊ እርዳታ የማከፋፈሉን ስራ ላይ አሉታዊ ጫና ማሳረፉም መግለጫው አመላክቷል።

ይሄም ሆኖ መንግስትና የረድኤት ድርጅቶች በአብዛኛው በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ሰብዓዊ እርዳታ ማዳረስ መቻላቸውን አስታውቋል።

ከሦስት ዙር በላይ በተደረገ ድጋፍ የማዳረስ ጥረትም በመንግስት ቢያንስ ለ 7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች ሰብዓዊ እርዳታ ማቅረብ መቻሉ ተገልጿል።

በታህሳስ ወር አጋማሽ እንደገና በተጀመረው የዓለም ምግብ ፕሮግራምና የሌሎች አጋር አካላት እገዛ በአማራ ፤በትግራይ፣ በሶማሌና በአፋር ክልሎች በድርቅ በተጠቁ አካባቢዎች ወደ 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ድጋፍ እንዲያገኙ ተደርጓል።

ይህ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት የቅድሚያ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ በጥር ወርም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጫው አመላክቷል።

ለጋሽ አካላትም ይሄንኑ እንቅስቃሴ ለማገዝ ትኩረት እንዲሰጡ በመግለጫው ጥሪ የቀረበ ሲሆን ወቅቱን የጠበቀ ምላሽ በገንዘብ ድጋፍና በሰብዓዊ እርዳታ ማቅረብ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑም ተመላክቷል።

በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን ተደራሽ ለማድረግም የተቀናጀ አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት አስፈላጊ መሆኑም ተገልጿል።

መንግስትና የረድኤት ድርጅቶች ሰብዓዊ እርዳታ በማድረስ በኩል ያላቸውን ልምድና የተጠናከረ የባለሙያ ስብስብ ለዚሁ ተግባር ለማዋል ዝግጁ መሆናቸውም መግለጫው አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም