የኢትየጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ምሽት ወደ ሞሮኮ እንደሚያቀና ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትየጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ምሽት ወደ ሞሮኮ እንደሚያቀና ተገለጸ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 30/2016(ኢዜአ)፦ የኢትየጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድኑ 22 ተጫዋቾችን በመያዝ የፊታችን ጥር 4 ቀን 2016 ዓ.ም ሞሮኮ ላይ ለሚያደርገው ጨዋታ ዛሬ ምሽት ወደ ሞሮኮ እንደሚያቀና ተገለጸ፡፡
አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የብሔራዊ ቡድኑን ዝግጅትና ጨዋታ አስመልክቶ ዛሬ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
11ኛው የፊፋ የሴቶች ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ በኮሎምቢያ አዘጋጅነት እ.አ. አ. ከነሐሴ 31 እስከ መስከረም 22, 2024 ይካሄዳል።
24 አገራት በሚሳተፉበት ውድድር አፍሪካ አራት አገራትን የማሳተፍ ኮታ የተሰጣት ሲሆን ኢትዮጵያም በማጣሪያ ውድድሩ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ደርሳለች።
ብሔራዊ ቡድኑ ከሞሮኮ ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ ከሶስት ሳምንት በላይ በአዲስ አበባ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን አሰልጣኝ ፍሬው ገልጿል።
ከሞሮኮ ጨዋታ በፊት ብሔራዊ ቡድኑ ሁለት የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግና ሞሮኮ ላይ ሰባት ቀናት ቀድሞ ሄዶ ዝግጅት ለማድረግ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ጥያቄ ቢያቀርብም አለመሳካቱን አመልክቷል።
የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን ያደረጋቸውን የወዳጅነት ጨዋታዎች በመመልከት ቡድኑን ለማዘጋጀት ጥረት መደረጉን አብራርቷል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን አሰልጣኙ ከብሩንዲና ኬንያ ጋር የወዳጅነት ጨዋታን ለማድረግ ታቅዶ እንደነበር ገልጸዋል።
ሆኖም ቡድኑ ከብሩንዲ የሴቶች ብሔራዊ ብድን ጋር ሊያደረግ የነበረው ጨዋታ ከመርሐ-ግብር አለመጣጣምና ለኬንያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የቀረበው ጥያቄ ደግሞ ኬንያ እንደማትችል በመግለጿ አለመሳካቱን አመልክተዋል።
ብሔራዊ ቡድኑ 22 ተጫዋቾችን በመያዝ የፊታችን ጥር 4 ቀን 2016 ዓ.ም ሞሮኮ ላይ ለሚያደርገው ጨዋታ ዛሬ ምሽት ወደ ሞሮኮ እንደሚያቀና ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የሞሮኮ አቻውን በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፈ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በፊፋ ከ20 በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ የሚሳተፍ ይሆናል።
ብሔራዊ ቡድኑ ከዚህ ቀደም በነበሩ የማጣሪያ ጨዋታዎች ኢኳቶሪያል ጊኒና ማሊን ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
11ኛው የፊፋ የሴቶች ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ 24 አገራት እንደሚሳተፉበት የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) አስታውቋል።