የባዮጋዝ ቴክኖሎጂ ስርጭት ማስፋፊያ ፕሮግራም የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋምና ምርታማነትን ማሳደግ ማስቻሉ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የባዮጋዝ ቴክኖሎጂ ስርጭት ማስፋፊያ ፕሮግራም የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋምና ምርታማነትን ማሳደግ ማስቻሉ ተገለጸ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 30/2016(ኢዜአ)፦ የባዮጋዝ ቴክኖሎጂ ስርጭት ማስፋፊያ ፕሮግራም ምርታማነትን በማሳደግ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋምና ጤናማ ማህበረሰብ መገንባት ማስቻሉን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
የኔዘርላንድስ ልማት ድርጅት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመተባበር ለሰባት ዓመታት ገቢራዊ ያደረገው ሶስተኛው ዙር የባዮጋዝ ቴክኖሎጂ ስርጭት ማስፋፊያ ፕሮግራም ማጠቃለያ መርሐ ግብር ዛሬ ተከናውኗል፡፡
ፕሮግራሙ በስምንት ክልሎች በሚገኙ 350 ወረዳዎች የዜጎችን ጤናማ አኗኗርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ተግባራዊ ሲደረግ የቆየ ነው፡፡
የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ እንዳሉት፤ ዝቅተኛ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ካላቸው ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ ከአህጉር ደግሞ አፍሪካ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ከ51 በመቶ እንደማይበልጥ ገልጸው፤ 90 በመቶ የሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል ምግብ የሚያበስለው በማገዶ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለማገዶ የደን መጨፍጨፍ ለአየር ንብረት መዛባት፤ ለካርበን ልቀት መጨመር፤ ለአፈር መሸርሸር፣ ለሰብል ምርታማነት መቀነስ ብሎም ለምግብ ዋስትና አለመረጋገጥ ምክንያት ነው ብለዋል፡፡
መንግስት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂን የስትራቴጂክ እቅዱ አካል በማድረግ የባዮጋዝ ቴክኖሎጂ ስርጭት ማስፋፊያ ፕሮግራም እየተገበረ መሆኑን አንስተዋል።
ላለፉት ሰባት ዓመታት በአውሮፓ ህብረት የገንዘብ ድጋፍ ከኔዘርላንድስ ልማት ድርጅት ጋር ሲሰራበት የቆየው ይህ ፕሮጀክት በገጠሩ ማህበረሰብ ዘንድ ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገቡን ገልጸዋል፡፡
የባዮጋዝ ቴክኖሎጂን ለማበልጸግ የቁም እንስሳት ተረፈ ምርት እና ውኃ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ በርካታ የቁም እንስሳት ያላት በመሆኗ ሥራውን ውጤታማ እንዳደረገው አስረድተዋል፡፡
በዚህም ከኃይል አቅርቦት በተጨማሪ የባዮጋዝ ተረፈ ምርቱን ለተፈጥሮ ማዳበሪያነት በመጠቀም የሰብል ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡
በኢትዮጵያ ከ28 ሺህ በላይ አባወራዎችና እማወራዎች እንዲሁም ከ180 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው፤ ከሁለት ሚሊዮን ቶን በላይ የተበከለ አየር ልቀትን ማስቀረት መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
በቀጣይም ከ140 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ የተፈጥሮ የአፈር ማዳበሪያ ማምረት የሚያስችል አቅም መገንባቱን በማመላከት፡፡
የኔዘርላንድስ ልማት ድርጅት ፕሮግራም አስተባባሪ የትናየት ግርማው፤ ፕሮጀክቱ ለጤናማ የምግብ ዝግጅት፤ የበካይጋዝ ልቀትን ለመከላከልና የግብርና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህም በኢትዮጵያ በስምንት ክልሎች ከመንግስት ሰራተኞች እስከ ግሉ ዘርፍና ማህበረሰቡ ድረስ እውቀት፣ ልምድና ቴክኖሎጂ እንዲስፋፋ መደረጉን አብራርተዋል፡፡
መንግስት የባዮጋዝ ቴክኖሎጂን የስትራቴጂው እቅድ አካል ማድረጉ የዘርፉን ውጤታማነት የበለጠ እንደሚያሳድገውም ነው የገለጹት፡፡
የባዮጋዝ ቴክኖሎጂን የማስተዋወቅ ሂደት እንዳለው የገለጹት አስተባባሪዋ፤ በሶስት ዙሮች በርካታ የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ህብረተሰቡ ጥቅሙን በአግባቡ ስለተረዳ የቴክኖሎጂው ገቢራዊነት እየሰፋ እንደሚሄድ ገልጸዋል፡፡
በአውሮፓ ህብረት የአረንጓዴ ልማት ትግበራ ቡድን መሪ ሮቤርቶ ሽሊሮ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የባዮጋዝ ቴክኖሎጂ ስርጭት ማስፋፊያ ፕሮግራምን በብቃት ተግብራለች ብለዋል፡፡
በዚህም ባለፉት ዓመታት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፤ ግጭትና ሌሎችም ችግሮችን በመቋቋም በባዮጋዝ ቴክኖሎጂ አበረታች ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ አተገባበር ውጤታማ አፈፃፀም እንዳላት የገለጹት ቡድን መሪው፤ ህብረቱ በቀጣይ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።