በኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ስርዓቱን የሚያዘመን እና አፈጻጸሙን ለማሳደግ ያለመ የሎጂስቲክስ ረቂቅ ማስተር ፕላን ተዘጋጀ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ስርዓቱን የሚያዘመን እና አፈጻጸሙን ለማሳደግ ያለመ የሎጂስቲክስ ረቂቅ ማስተር ፕላን ተዘጋጀ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 30/2016(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ስርዓቱን የሚያዘመን እና አፈጻጸሙን ለማሳደግ ያለመ የሎጂስቲክስ ረቂቅ ማስተር ፕላን ተዘጋጀ።
በአውሮፓ ሕብረት የገንዘብ ድጋፍ 'ዲቲ ግሎባል' በተሰኘ አማካሪ ድርጅት በኩል የተጠናው የሎጂስቲክስ ማስተር ፕላን የመጀመሪያ ምዕራፍ ረቂቅ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ ውይይት ተካሂዷል።
የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ደንጌ ቦሩ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ሎጂስቲክስ ለሁሉም ኢኮኖሚ ዘርፎች የደም ስር በመሆኑ የዘርፉን ዕቅድ በየጊዜው መከለስ እና ማሻሻል ይጠይቃል።
መንግሥት ጠንካራ የሎጂስቲክስ ስርዓት ለመገንባት ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ቀርጾ ወደስራ መግባቱን ተናግረዋል።
በስትራቴጂው ከተቀመጡ መሰረታዊ ጉዳዮች መካከል የሎጂስቲክስ ማስተር ፕላን ማዘጋጀት አንዱ በመሆኑ ለመጪዎቹ 30 ዓመታት የሚኖረውን የሎጂስቲክስ ጉዞ በአግባቡ የሚጠቁም ረቂቅ ማስተር ፕላን መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ማስተር ፕላኑ የሀገሪቷን ሎጂስቲክስ አፈጻጸም በማጎልበት የብዝሀ ኢኮኖሚ ግንባታን የሚያግዝ፣ የዘርፉን ክፍተቶች በመለየትና የቀጣይ መዳረሻን የሚያመላክት ነው ብለዋል።
የተሟላ የሎጂስቲክስ መረጃ እንዲኖር የሚያስችል፣ በዘርፉ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ለመተግበርና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ የጋራ አረዳድ እንዲያዝ መደላድል የሚፈጥር ስለመሆኑም ጠቁመዋል።
ከማስተር ፕላኑ ጥቁምታዎች መካከል አማራጭ ወደብ መጠቀም አንዱ የመፍትሔ ሃሳብ እንደሆነ ጠቅሰው፣ በቅርቡ የተደረገው የኢትዮ-ሶማሌላንድ የመግባቢያ ስምምነትም ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
አማራጭ ወደቦችን መጠቀም በወጭና ገቢ ንግድ ከዋጋ፣ ከጊዜ እና ከምርት ጥራት አኳያ ተወዳዳሪነትን የሚጨምር እና የሀገሪቷን ኢኮኖሚ ዕድገት የሚያሳልጥ እንደሆነ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አብዱልበር ሸምሱ፥ ረቂቅ ማስተርፕላኑ በተቋም ደረጃ መገምገሙን ገልጸው፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተደረገበት መሆኑን ተናግረዋል።
ማስተርፕላኑ የዘርፉን ማነቆዎች ለይቶ መፍትሄ ለማስቀመጥ፣ የሎጂስቲክስ ስርዓቱን በዲጂታላይዜሸን ለማዘመን እና ጸጋዎችን በመለየት በተቀናጀ አግባብ ለይቶ ለመጠቀም እንደሚረዳ ገልጸዋል።
የዲቲ ግሎባል ድርጅት ተወካይ ዶክተር ማርክ ፔርሰን፥ ሎጂስቲክስን ማዘመን ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገት ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል።
ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ማስተር ፕላን ማዘጋጀቷ፤ የዘርፉን ችግሮች በመለየት ለመፍታት እንደሚያስችላት ነው የተናገሩት።