ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ የተፈራረሙት የመግባቢያ ሥምምነት በርካታ ትሩፋቶች ይዞ የሚመጣ ታሪካዊ ክስተት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ የተፈራረሙት የመግባቢያ ሥምምነት በርካታ ትሩፋቶች ይዞ የሚመጣ ታሪካዊ ክስተት ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 30/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ የተፈራረሙት የመግባቢያ ሥምምነት የኢትዮጵያውያን የረዥም ጊዜ ጥያቄ የመለሰና በርካታ ትሩፋቶች ይዞ የሚመጣ ታሪካዊ ክስተት መሆኑን የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ገለጸ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ( ዶ/ር) እና የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ሥምምነት መፈራረማቸው ይታወቃል።
በሥምምነቱ መሠረት ኢትዮጵያ ወደብና የጦር ሰፈር ለመገንባት የሚያስችላትን ቦታ በሊዝ የምታገኝ ሲሆን ሶማሌላንድ ደግሞ ከኢትዮጵያ የልማት ኩባንያዎች ድርሻ እንደምታገኝ ተገልጿል።
የመግባቢያ ሥምምነቱን በተመለከተ የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል።
በመግለጫው የፈዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ወጣት መሐዲን ናስር ፤ ሥምምነቱ መንግሥት የኢትዮጵያን መሻቶች በትብብር፣ በሰጥቶ መቀበልና በሰላማዊ መንገድ ብቻ ለማሳካት ያለውን እምነት በተግባር ያሳየበት ነው ብሏል።
ሥምምነቱ የኢትዮጵያውያን የዘመናት ቁጭት ለማከም የሚያስችል አጋጣሚን የፈጠረ በመሆኑ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚያስደስት ታሪካዊ ክስተት ነው ሲል ገልጿል።
የአገራችን ወጣቶች የረዥም ጊዜ የኢኮኖሚ ጥያቄ የሆነውን የወደብ ጥያቄ የጋራ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ ማሳካት የተቻለበትሥምምነት መሆኑንም አስታውቋል።
ይህም ለአፍሪካ ቀንድ ልማትና ብልፅግና ትልቅ እምርታ እንዳለው ጨምሮ ተናግሯል።
ይህ በዘመናት አንዴ የሚከሠት የታሪክ አጋጣሚ መሆኑን የተናገሩት አቶ መሐዲን ይህን አጋጣሚ በመጠቀም የኢትዮጵያ ወጣቶችን ለአገራችን እድገት በጋራ ልንሰራ ይገባል ነው ያለው።
ለመግባቢያ ሥምምነቱ ተግባራዊነት የኢትዮጵያ ወጣቶች የሚጠበቅባቸውን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ፌዴሬሽኑ አረጋግጧል።