በክልሉ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራው ዘላቂ ጠቀሜታ በሚሰጥ አግባብ ይከናወናል - ቢሮው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራው ዘላቂ ጠቀሜታ በሚሰጥ አግባብ ይከናወናል - ቢሮው

ደሴ፤ ታህሳስ 30/2016 (አዜአ)፡-በአማራ ክልል በዘንድሮው የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራ የተራቆቱና የተመናመኑ አካባቢዎችን በማልማት በዘላቂነት ጥቅም እንዲሰጡ በሚያደርግ አግባብ እንደሚሰራ የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የ2016 ዓ.ም የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራዎች የምክክር መድረክ በደሴ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ድረስ ሳህሉ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራውን በማጠናከር ግብርናውን ማዘመንና ኢኮኖሚውን ማነቃቃት ይገባል።
በዚህም በክልሉ ባለፉት ዓመታት የተሰሩ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራዎች የአፈር ለምነት መጠበቅ ምርታማነት ማሳደግ፣ የደን ሽፋን መጨመር፣ የስራ እድል መፍጠርና ሌሎችም ጠቀሜታዎች ማስገኘቱን ገልጸዋል።
በመሆኑም በዘንድሮው ዓመትም በክልሉ የተራቆቱና የተሸረሸሩ ገደላማ አካባቢዎችን ሁሉ በማልማት በዘላቂነት ጠቀሜታ እንዲሰጡ በሚያስችል አግባብ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ዘርፉን በባለሙያ እንዲመራ በማድረግ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት በመጠበቅና አልምቶ ለትውልድ በማስተላለፍ ከድህነት ለመላቀቅ ሁሉም የድርሻቸውን እንዲወጣም አሳስበዋል።
የቢሮው ምክትል ሃላፊ ዶክተር አልማዝ ጊዜው በበኩላቸው፤ የተራቆቱ አካባቢዎችን በተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራ እንዲያገግሙና እንዲለሙ በማድረግ ጠቀሜታ እንዲሰጡ እየተደረገ ይገኛል።
በዚህም ካለፉት ዓመታት ልምድ በመውሰድ በዘንድሮው የበጋ ወራትም በክልል በ9 ሺህ 60 ተፋሰሶች 376 ሺህ ሄክታር በሚሸፍን መሬት የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራ ለማከናወን ቅደመ ዝግጅት ተጠናቋል።
ለዚህም ከ307 ሺህ በላይ ቀያሽ አርሶ አደሮችና ከ3 ሚሊዮን በላይ የተለያየ የልማት መሳሪያ መለየቱን ገልጸዋል።
በአማካይ ለ23 ቀናት በሚቆየው ልማቱ ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍል ይሳተፋል ተብሎ እንደሚጠበቅም አብራርተዋል።
ባለፉት ዓመታት በተሰሩ ስራዎች የአፈር ለምነትን መጠበቅ በአንድ ሄክታር መሬት ከ2 እስከ 4 ኩንታል ምርታማነት መጨመር እንደተቻለም አመልክተዋል።
እንዲሁም በተፋሰሶች ከ24 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉን ጠቁመው፤ ዘንድሮም በቅንጅት ውጤታማ በማድረግ የክልሉን ህዝብ ሁለተናዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል።
ከምክክሩ ተሳታፊዎች መካከል የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ አዲሱ ቡላ እንዳሉት በዘንድሮው የበጋ ወራት በዞኑ ከ20 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ይከናወናል።
ለዚህም በየደረጃው የንቅናቄ መድረክ እየተከናወነ ሲሆን ልማቱ በ334 ተፋሰሶች ላይ እንደሚከናወንም ገልፀዋል።
በአማራ ክልል ባለፈው ዓመት 357 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራ መከናወኑን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያሳያል።
በመድረኩ የክልሉ፣ የምስራቅ አማራ ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም የሴክተር አመራሮች እየተሳተፉ ይገኛሉ።