አገልግሎቱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከተሞችን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ማሻሻሉን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
አገልግሎቱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከተሞችን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ማሻሻሉን አስታወቀ
ቦንጋ ፤ታኀሣሥ 30/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት 80 ሚሊዬን ብር በጀት በመመደብ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከተሞችን የኃይል አቅርቦት ማሻሻሉን አስታወቀ።
በአገልግሎቱ የደቡብ ምዕራብ ክልል ሪጅን ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ብርሃኑ ገብሬ ለኢዜአ እንደገለጹት አገልግሎቱ በመደበው በጀት በክልሉ የኃይል መቆራረጥ ችግር የሚስተዋልባቸው መስመሮችን አሻሽሏል።
በተለይም የኤሌክትሪክ አገልግሎቱን አስተማማኝና ተደራሽ ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት ከግብ ለማድረስ ባለፉት ስድስት ወራት ከፍተኛ የኃይል መቆራረጥ ችግር በሚስተዋልባቸው መሥመሮች የማሻሻያ ሥራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።
በክልሉ የኃይል አቅርቦትን ለማሻሻል የተደረገው እንቅስቃሴ ከሚዛን ሰብስቴሽን እስከ ጀሙ እንዲሁም ከሺሺንዳ፣ ቢጣና ወሺ ያለው ከ300 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት እንደተሸፈነ ገልጸዋል።
በዚህም የክልሉ ስምንት ከተሞች ተጠቃሚ መሆናቸውን አመልክተው፣ ሥራው በሌሎች አካባቢዎች እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
በአገልግሎቱ የደቡብ ምዕራብ ሪጅን የዲስትሪቢውሽን፣ የኮንስትራክሽን፣ የኦፕሬሽንና የጥገና ሥራ ኃላፊ አቶ እስራኤል ሐብታሙ የክልሉ ተጋልጋዮች የሚያነሱትን ቅሬታ ለመፍታት በተደረገው እንቅስቃሴ ውጤታማ አፈጻጸም መከናወኑን ተናግረዋል።
ከዚህም ከ700 በላይ የኮንክሪት ምሰሶዎችን በመትከል በከተሞቹ ይስተዋል የነበረውን የኃይል መቆራረጥ ከ50 እስከ 70 በመቶ ለመቀነስ ተችሏል ብለዋል።
በክልሉ ከተሞች የሚያጋጥመው የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ችግር የመልካም አስተዳደር ምንጭ ሆኖ መቆየቱን የተናገሩት በሪጅኑ የጨና ደንበኞች አገልግሎት መስጫ ማዕከል ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደለ ዘውዴ ናቸው።
አሁን ላይ ከፍተኛ ጫና የነበረበትን የጨና መስመር የኃይል አቅርቦት ለማሻሻል በተከናወኑ ሥራዎች አገልግሎት አሰጣጡ የተሻሻለ ሲሆን፣ የኃይል መቆራረጥ ችግር መቀነሱንና የተገልጋዮች እርካታ መጨመሩን ገልጸዋል።
በዋቻ ማጂ ከተማ የወፍጮ ቤት ባለቤት አቶ አክሊሉ ተክሌ የኤሌክትሪክ የኃይል ማነስና መቆራረጥ ሥራቸውን በተገቢው መንገድ እንዳይሰሩ ችግር ሲፈጥርባቸው መቆየቱን አስታውሰዋል።
አሁን ላይ ችግሩ በመፈታቱ ሥራቸውን በአግባቡ ለማከናወን መቻላቸውን ተናግረዋል።
በከተማቸው የኤሌከትሪክ አገልግሎት ከሚያገኙበት ይልቅ የማያገኙበት ጊዜ እንደሚበልጥና አቅርቦቱ ተመልሶ ሲቀጥል የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች እንደሚቃጠሉባቸው የተናገሩት የዋቻ ከተማ ነዋሪው አቶ ሐብታሙ ከበደ ናቸው።
አገልግሎቱ ችግሩን ለማቃለል ያደረገው እንቅስቃሴ ለቅሬታቸው ምላሽ መስጠቱንና እሳቸውን ጨምሮ ለአካባቢው ነዋሪዎች እፎይታን እንደሰጠ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደቡብ ምዕራብ ሪጅን ከ80 ሺህ ለሚልቁ ደንበኞች አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ የተቋሙ መረጃ ያመለክታል።