ቀጥታ፡

ኢትዮ-ቴሌኮም ለኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከል የሚውል ዲጂታል የድጋፍ ማሰባሰቢያ አማራጮችን አዘጋጀ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 30/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮ-ቴሌኮም ለኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከል የሚደረገውን ድጋፍ ቀላልና ቀልጣፋ ማድረግ የሚያስችል የዲጂታል ድጋፍ ማድረጊያ አማራጮችን ማዘጋጀቱን አስታወቀ።

ኢትዮ- ቴሌኮም የዲጂታል የመርጃ አማራጮችን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን ማብራሪያ ሰጥቷል።

የኢትዮ- ቴሌኮም የኮሙኑኬሽን ዲቪዥን ዳይሬክተር ወይዘሮ አዜብ መለሰ መርሃ ግብሩን አስመልክተው እንዳሉት፤ ኢትዮ- ቴሌኮም በአገሪቱ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ የዜጎችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ለማቅለል ጥረት እያደረገ ይገኛል።

ከዚህ ጎን ለጎን ማህበራዊ ሃላፊነቱን በመወጣት አጋርነቱን በተግባር እያሳየ ስለመሆኑም አንስተዋል።

ከጥር 1 ቀን ጀምሮ ለአንድ ወር የሚቆይና ገቢው ለኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከል የሚውል የድጋፍ መርሃ ግብሮችን አዘጋጅቷል ብለዋል።

መርሃ ግብሩ የኢትዮ- ቴሌኮምን የዩትዩብና የፌስ ቡክ  ገጾችን ሰብስክራይብና ፎሎ በማድረግ በአንድ ሰው 30 ብር ወደ ማዕከሉ ገቢ የሚያደረግበት ነው።

በተጨማሪም ኢትዮ-ቴሌኮም ይፋ የሚያደርጋቸውን መተግበሪያዎችና መሠል ሁነቶችን በማህበራዊ ትስስር ገጾች አንድ መረጃን በሚያጋራ ሰው 10 ብር ወደ ማዕከሉ ገቢ ይሆናል ነው ያሉት።

ለማዕከሉ ለገቢ ማሰባሰቢያነት እንዲውል ታስቦ በተዘጋጀው 67 10 የነፃ መስመር  በሚላኩ ድጋፎች ላይም እንዲሁ 10 በመቶ ጭማሪ በማድረግ ሃላፊነቱን ይወጣል ብለዋል። 

የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ህሩይ አሊ በበኩላቸው ማዕከሉ ላለፉት 35 ዓመታት የነፃ የልብ ቀዶ ህክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

በዚህም በልብ ህመም ምክንያት የሚሰቃዩ በርካታ ህፃናት  ጤናቸው እንዲመለስ በማድረግ ሀላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን አብራርተዋል።

ለዚህም በርካታ አጋር አካላት፣ ግለሰቦችና የተለያዩ ተቋማት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ የጎላ ሚና እንዳለው አንስተዋል።

በተጨማሪም በኢትዮ-ቴሌኮም አማካኝነት 67 10 እና በቴሌ ብር የተዘረጋው አማራጭ ማዕከሉን በእጅጉ እያገዘ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። 

አሁን ደግሞ ኢትዮ-ቴሌኮም የተቋሙን የማህበራዊ ትስስር ገፆች በመጠቀም ለማዕከሉ ድጋፍ የሚደረግበትን አማራጭ መዘርጋቱ ተቋሙን ለመርዳት ለሚፈልጉ ዜጎች የተሻለ አማራጭ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመሆኑም ህብረተሰቡ ለአንድ ወር የሚቆየውን ይህን የዲጂታል የድጋፍ መስጫ አማራጭ በመጠቀም  እንደ ሁልጊዜው ቀና ትብብሩን እንዲያደርግ ዋና ስራ አስኪያጁ ጥሪ አቅርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም