የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ካዛብላንካ ሞሮኮ የጭነት በረራ አገልግሎት ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ካዛብላንካ ሞሮኮ የጭነት በረራ አገልግሎት ጀመረ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 30/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ 35ኛውን የጭነት በረራ አገልግሎቱን በሞሮኮ ካዛብላንካ መጀመሩን አስታወቀ።
የበረራ አገልግሎቱን መጀመር አስመልክቶ የኢትዮጵያ አየርመንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው እንዳሉት ወደ ካዛብላንካ ሞሮኮ የተጀመረው አዲሱ አገልግሎት በሰሜን አፍሪካ ማግሪብ ቀጣና ወደ አለም አቀፉ የጭነት በረራ አገልግሎት መዳረሻዎችን ያካተተ አዲስ ምዕራፍን የከፈተ ነው።
የበረራው መጀመር በአፍሪካ ያሉትን የዕቃ ጭነት መዳረሻ ቁጥር 35 ሲያደርስ፤ በተመሳሳይ አየር መንገዱ በእቃ ጭነት አገልግሎት ዘርፍ አስተማማኝ እና ቀልጣፋ አገልግሎት ለማቅረብ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጭነት በረራ መዳረሻዎች ብዛት ከአፍሪካ ቀዳሚ እና በዓለም የአየር የዕቃ ጭነት አገልግሎት መስክ ቁልፍ ሚና በመጫወት ላይ የሚገኝ እንደመሆኑ የዓለም ንግድ እና ሸቀጦች ፍሰትን ለማሳለጥ አዳዲስ የጭነት መስመሮችን በመክፈት አገልግሎቱን በዓለም ዙሪያ ማስፋፋቱን እንደሚቀጥል ጠቅሰዋል።
ወደ ካዛብላንካ የሚደረገው የጭነት በረራ በዘመናዊው እና ከ100 ቶን በላይ የመሸከም አቅም ባለው ቦይንግ 777-200F የእቃ ጭነት አውሮፕላን የሚደረግ መሆኑን ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።