ቀጥታ፡

አብርሆት ቤተ መጻሕፍት የአለም አቀፉን የሲልክ ሮድ የላይብረሪዎች ጥራት ጥምረትን ተቀላቀለ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 30/2016(ኢዜአ)፦ አብርሆት ቤተ መጻሕፍት የአለም አቀፉን የሲልክ ሮድ ቤተ መጻሕፍት ጥራት ጥምረትን ተቀላቀለ።

ቤተመጻሕፍቱ ይህንን ጥምረት የተቀላቀለው ከተገነባ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ጥራትና አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት በመቻሉ መሆኑን መቀመጫውን ቻይና ያደረገው የሲልክ ሮድ አለም አቀፍ የቤተመጻሕፍት ጥምረት ይፋ አድርጓል።

አለም ላይ ከተገነቡት ቤተመጻሕፍት መካከል አብርሆት ቤተመጻሕፍት በአጭር ጊዜ የአለም አቀፉን ማህበረስብ የጥናት፣ የምርምር፣ የፈጠራ እንደዚሁም የጥንታዊ መፅሃፍት መገኛ በመሆን ትኩረት መሳብ እንደቻለ የገለፀው ተቋሙ የኢትዮጵያ ቤተ መጽሐፍት ብቻ ሳይሆን የደመቀ የእውቀት መዳረሻ ቦታ ነው ሲል ገልፆታል።

ይህም 43ኛ ቤተመጻሕፍት ተቋማት ጥምረት ሆኖ መመዝገብ መቻሉን የሲልክ ሮድ አስታውቋል።

አብርሆት ቤተመጻሕፍት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሃሳብ አመንጭነትና ድጋፍ ለምረቃ በቅቶ አንፀባራቂ አገልግሎቶችን እየሰጠ እንደሚገኝም የአለም አቀፉ የቤተመጻሕፍት ጥምረት ገልጿል።

በአሁኑ ጊዜ ሶስት መቶ ሽህ በላይ የሃገር ውስጥ የጥናትና ምርምር ውጤቶች፣መቶ ሃያ ሽህ በላይ አለም አቀፍ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን የያዘ ከመሆኑም ባሻገር በውስጡ ከአንድ ነጥብ አራት ሚሊየን በላይ መፅሃፍቶችን መያዙንም ተቋሙ በመረጃው አስታውቋል።

የአብርሆት ቤተመጻሕፍት አስገራሚ ግንባታና አቀማመጥ እንደዚሁም ዙሪያ ግቢው የተላበሰው አረንጓዴያማ ገፅታ የተቋሙን ሞገስ ከፍ ከማድረጉም በላይ የዜጎች የንባብ ፍላጎት እንዲነሳሳ እንደሚጋብዝም የአለም አቀፉ የቤተመጻሕፍት ጥምረት ሲልክ ሮድ አያይዞ ገልጿል።

አብርሆት ቤተመጻሕፍት በቀን ከ10 ሽህ በላይ አንባቢዎችን በማስተናገድ የ24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጥ ግዙፍ ተቋም ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም