ቀጥታ፡

አሲዳማ መሬትን ማከም የሚያስችል ምጥን ማዳበሪያ በአርሶ አደር ማሳ የማላመድ ተግባር  እየተካሄደ መሆኑ ተገለጸ

ዲላ ፤ ታህሳስ 30/2016 (ኢዜአ)፦ ከኖራ በተጨማሪ አሲዳማ መሬትን ማከም የሚያስችል አማራጭ ምጥን ማዳበሪያ በአርሶ አደር ማሳ የማላመድና የማስፋት ሥራ እያካሄደ መሆኑን የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

በጌዴኦ ዞን ቡሌ ወረዳ አሲዳማ መሬትን ማከም የሚያስችል አማራጭ ምጥን ማዳበሪያ ሰርቶ ማሳያ የመስክ ምልከታ ተካሂዷል።

በኢንስቲትዩት የወንዶ ገነት ምርምር ማዕከል የአፈር ደህንነትና ጤንነት ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር አሸናፊ ንጉሴ በወቅቱ እንዳሉት ኖራን ጨምሮ የተለያዩ ሂደቶችን በመጠቀም አሲዳማና ጨዋማ መሬትን በማከም ለግብርና ልማት እያዋለ ነው።

ኢንስቲትዩቱ ከኖራ በተጨማሪ አሲዳማ መሬትን ለማከም አማራጭ መንገዶች ያፈላለገባቸው ምርምሮች ማካሄዱን አስታውሰዋል።

በዚህም በምርምር 18 ምጥን የተሰኙ የአፈር ማዳበሪያዎች ተለይተው 11ዱ በሀገር ደረጃ ፍተሻ እንደተደረገባቸው መሆኑን ዶክተር አሸናፊ አስረድተዋል።

በነዚህም በአራት ዋና ዋና ሰብሎች ላይ ተሞክሮ ወደ ትግበራ ተገብቷል ብለዋል።

ማዕከሉ በጌዴኦ ዞን ቡሌና ገደብ ወረዳዎች በኩታ ገጠም አርሶ አደሮች የገብስ ማሳ ላይ የተፈተሸው አማራጭ ምጥን ማዳበሪያ ሙከራ ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በሄክታር 28 ኩንታል ምርት መገኘቱንና ይህም በወረዳዎቹ በአማካይ ከሚገኘው ምርት የ10 ኩንታል በላይ ብልጫ እንዳለው ተመራማሪው አስታውቀዋል።

ውጤቱ በአነስተኛ የሰው ኃይል ለማልማትና ወጪን በቆጠበ መልኩ ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ፣ በአሲድ የተጠቃ መሬት ወደ ምርት ለማስገባት ድርሻው የጎላ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ከኖራ በተጨማሪ አሲዳማ መሬትን ማከም የሚያስችል አማራጭ ማዳበሪያ በአርሶ አደር ማሳ የማላመድና የማስፋት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ዶክተር  አሸናፊ ገልጸዋል።


 

የጌዴአ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ታጠቅ ዶሪ አሲዳማ መሬትን ለማከም ኖራን ለመግዛት፣ ለማከፋፈልና ጥቅም ላይ ለማዋል ከሚያስፈልገው ወጪ በተጨማሪ የአርሶ አደር ጉልበት በስፋት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል። 

ይህንን ወጪና ድካም የሚያስቀርና ምርታማነትን የሚጨምር አማራጭ ዘዴ መገኘቱ ጠቀሜታው ዘርፈ ብዙ ነው ብለዋል።

አማራጭ የምጥን ማዳበሪያ በቡሌ ወረዳ በገብስ ማሳ ላይ ተሞክሮ ውጤት ማምጣቱ በመስክ ምልከታው ማረጋገጣቸውን የተናገሩት ኃላፊው፣ መምሪያው ማዳበሪያውን በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውል ድጋፍ  እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የቡሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ በራቆ በራሶ በበኩላቸው በወረዳው ከአምስት ሺህ ሄክታር በላይ ሊለማ የሚችል መሬት በአሲዳማነት በመጠቃቱ ከምርት ውጭ ሆኖ መቆየቱን ገልጸዋል።

በ2015/16 ምርት ዘመን ከ1 ሺህ 800 ሄክታር  አሲዳማ መሬት በማከም ለግብርና ልማት መዋሉን ገልጸው፣ይህም ልማቱን ለማስፋፋት ያግዛል ብለዋል።

በወረዳው የኢላልቻ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ማሪያም ዋሬ፣ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ መሬታቸውን በኖራ በማከም ገብስና ስንዴን ጨምሮ ሰብል እያመረቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በ2015/16ምርት ዘመን በማዕከሉ የታገዙ ሰባት አርሶ አደሮች ጋር በኩታ ገጠም አምስት ሄክታር መሬት ላይ አማራጭ ምጥን ማዳበሪያ ተጠቅመው ገብስ በማምረት የተሻለ ምርት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

አማራጩ ማዳበሪያ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ፣አርሶ አደሮች አሲዳማ መሬትን በኖራ ለማከም  የሚያወጡትን ጉልበትና ወጪ ለመቀነስ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው አመልክተዋል። 

በቀጣይም ሌሎች አርሶ አደሮች ማዳበሪያውን በመጠቀም ማሳቸውን እንዲያለሙ ድጋፍ አደርጋለሁ ብለዋል።

በመስክ ምልከታው ላይ የኢንስቲትዩቱ አመራር አባላት፣ ተመራማሪዎች፣ አርሶ አደሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም