ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ10ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ይጀመራል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 30/2016(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ10ኛ ሳምንት የውድድር መርሐ ግብር የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ኢትዮጵያ ቡና ከሻሸመኔ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

በ14 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች በሁለቱ ሲያሸንፍ በሁለቱ ሽንፈት ገጥሞታል። አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።

ተጋጣሚው ሻሸመኔ ከተማ በበኩሉ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች በሁለቱ ሲሸነፍ በሶስቱ ነጥብ ተጋርቷል።

በሊጉ እስከ አሁን ምንም ጨዋታ ያላሸነፈው ሻሸመኔ ከተማ በ3 ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።


 

ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ የሚደረገው ጨዋታ ሲዳማ ቡናና አዳማ ከተማን ያገናኛል።

ሲዳማ ቡና በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች በሁለቱ ድል ሲቀናው በሁለቱ ተሸንፏል። በአንዱ ነጥብ ተጋርቷል።

በ11 ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በ13 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አዳማ ከተማ ባለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች በሁለቱ አሸንፎ በሁለቱ ተሸንፎ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 10ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ነገም ቀጥሎ ሲውል መቻል ከሃዋሳ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት፤ ሀዲያ ሆሳዕና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከምሽቱ 12 ሰዓት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።


 

የሊጉ የ10ኛ ሳምንት ጨዋታዎች እስከ ጥር 3 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያሉ።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ23 ነጥብ ሊጉን እየመራ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም