የባህር በር ስምምነቱ ለሀገር እድገትና ዘላቂ ጥቅም በማሰብ የመንግሥት በሳል አመራር የታየበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የባህር በር ስምምነቱ ለሀገር እድገትና ዘላቂ ጥቅም በማሰብ የመንግሥት በሳል አመራር የታየበት ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 29/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት ከሱማሊ ላንድ ጋር ያደረገችው የመግባቢያ ስምምነት ለሀገር እድገትና ዘላቂ ጥቅም በማሰብ የመንግሥት በሳል አመራር የታየበት መሆኑን የኢትዮጵያ መምህራን ማኀበር ገለጸ።
በመግባቢያ ስምምነቱ መሰረት የባህር በር ተጠቃሚ ለመሆን በሚደረገው ሂደት ማህበሩ በመደገፍ የሚጠበቅበትን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጧል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የሶማሊ ላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወቃል።
በሥምምነቱ መሠረት ኢትዮጵያ ወደብና የጦር ሰፈር ለመገንባት የሚያስችላትን ቦታ በሊዝ የምታገኝ ሲሆን ሶማሊ ላንድ ደግሞ ከኢትዮጵያ የልማት ኩባንያዎች ድርሻ የምታገኝ ይሆናል።
የተደረሰው ስምምነት የሰጥቶ መቀበል መርህን በመከተል የህዝቦችን በትብብር ማደግን የሚያረጋግጥና ማንንም የማይጎዳ መሆኑ ተነስቷል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ለኢዜአ መግለጫ የሰጡት የኢትዮጵያ መምህራን ማኀበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሃንስ በንቲ፤ ካለን ኃብት አጋርተን የጎደለንን ለማግኘት ከሶማሊላንድ ጋር የተፈረመው ሥምምነት ለአገር የሚበጅ ነው ብለዋል።
የተደረሰው ሥምምነት ለሀገር እድገትና ዘላቂ ጥቅም በማሰብ የመንግሥት በሳል አመራር የታየበት መሆኑን ጠቅሰው ለተግባራዊነቱ በመደገፍ ማህበሩ የሚጠበቅበትን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በዚህ ረገድ የትምህርት ማኀበረሰቡ መረጃና ሰነዶች ላይ ተመስርቶ ዜጎችን ማስገንዘብ ይኖርበታል ሲሉም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያና ሱማሊ ላንድ መካከል የተፈረመው ሥምምነት ሠላማዊ መንገድን የተከተለ በመሆኑ ለሌሎች አገራት ሥጋት ሊሆን አይገባም ሲሉም ተናግረዋል።
በመሆኑም በተለያዩ ዓለም አገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች በየደረሱበት ሁሉ ይህን እውነታ ማስገንዘብ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
የባህር በር ስምምነት የሁለቱን ወገኖች የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲ፣ የፀጥታ እና የኢኮኖሚ ትብብር የሚያጠናከር መሆኑ ታምኖበታል።