የምዕራብ አርሲ ዞን አርሶ አደሮች የቢራ ገብስን በኩታ ገጠም በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የምዕራብ አርሲ ዞን አርሶ አደሮች የቢራ ገብስን በኩታ ገጠም በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገለጹ
ታህሳስ 29/2016 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ አርሲ ዞን አርሶ አደሮች የቢራ ገብስን በኩታ ገጠም በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገለፁ።
በምዕራብ አርሲ ዞን በሻሸመኔ ወረዳ ሆሳ ሲምቦ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መርጋ ገመዳ እንደተናገሩት የቢራ ገብስን በኩታ ገጠም በማልማት የተሻለ ምርትና ገቢ እያገኙ ነው።
'ሶፍሌት ማልት' የብቅል ፋብሪካ በሚያደርግላቸው ድጋፍ ያመረቱትን የቢራ ገብስ በቀጥታ ለፋብሪካው በማቅረብ የተሻለ ገቢ ማግኘት መቻላቸውንም ተናግረዋል።
አርሶ አደር መርጋ "ከዚህ ቀደም በደላላ ምክንያት የሚደርስብንን ጫናና ሌሎች እንግልቶች ያስቀረ በመሆኑ የተሻለ ተጠቃሚ እንድንሆን አስችሎናል" ብለዋል።
ቀደም ሲል በ1 ሄክታር መሬት ላይ ሲያለሙ የነበረውን የቢራ ገብስ አሁን ላይ ወደ 5 ሄክታር መሬት በማስፋፋት ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እየሰሩ መሆኑን ተናግረው ዘንድሮ በሄክታር 40 ኩንታል እንደሚያገኙ ተናግረዋል።
አርሶ አደር ከማል ሀጂ በበኩላቸው ቀደም ሲል በስፋት ሲያለሙ የነበረው ድንች እንደነበር ጠቁመዋል።
የ'ሶፍሌት ማልት' የብቅል ፋብሪካ የቢራ ገብስን በመስመር በመዝራት፣ ማሳቸውን በአግባቡ በመንከባከብና በማረም በሄክታር እስከ 40 ኩንታል ምርት በማግኘት ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ ገልጸዋል።
የ'ሶፍሌት ማልት' የብቅል ፋብሪካ ምዕራብ አርሲ ዞን አስተባባሪ አቶ መዝገቡ ኪሲ፣ የተሻሻለና ምርታማ የቢራ ገብስ ዝርያ በማባዛት በርካታ አርሶ አደሮች በልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከዚህ በፊት ከውጪ ይገባ የነበረው የብቅል ገብስን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት መቻሉን ገልጸው ይህ ውጤት የውጪ ምንዛሪን ከማስቀረት አንጻር ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።
የምዕራብ አርሲ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ሀላፊ አቶ ይሳቅ ገመዳ በበኩላቸው ዞኑ በቢራ ገብስ ልማት ያለውን አቅም ለመጠቀም ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አውሰተዋል።
በአካባቢው የሚለማው መሬትና የተሳታፊ አርሶ አደሮች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልጸው በ2015/2016 ምርት ዘመን በዞኑ በ111 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የቢራ ገብስ ልማት እየተካሄደ ይገኛል ብለዋል።
በዞኑ በቢራ ገብስ ከለማው ማሳ በአማካይ በሄክታር ከ35 እስከ 40 ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የስራ ኃላፊዎች በምዕራብ አርሲ ዞን በኩታ ገጠም የለማውን የቢራ ገብስ መጎብኘታቸው ይታወሳል።